ሱዳን በጠቅላይ ሚኒስትሯ ላይ የግድያ ሙከራ የፈጸሙትን ሰዎች ለመያዝ የወዳጅ ሀገራትን እርዳታ ጠየቀች
ሱዳን በጠቅላይ ሚኒስትሯ ላይ የግድያ ሙከራ የፈጸሙትን ሰዎች ለመያዝ የወዳጅ ሀገራትን እርዳታ ጠየቀች
የሱዳን ብሔራዊ የጸጥታና መከላከያ ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ላይ የግድያ ሙከራ የፈጸሙ አካላትን ለመፈለግ የሚደረገውን ጥረት ጎረቤት ሀገራት እንዲያግዙ ወሰነ፡፡
በሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሰብሳቢው አብደል ፋታህ አልቡርሃን ሰብሳቢነት በተደረገው አስቸኳይ ሰብሰባ ትናንትና የከሸፈውን የግድያ ሙከራ ማን እንደፈጸመው ለማወቅ እየተሰራ ላለው ስራ ወዳጅ ሀገራት ትብብር እንዲያደርጉ ተወስኗል፡፡
በሱዳን የሀገር ውስጥ ሚኒስትር አል ታሪፍ ዳፋላህ ኢድሪስ የተነበበው መግለጫ እንደሚያስረዳው የመንግስት ተቋማት አንድነታቸውን በማጠናከር የሀገርን ሰላም የሚነሱ የሽብር ድርጊቶችን መመከት አለባቸው ተብሏል፡፡
የጸጥታ ምክር ቤቱ በትናንትናው ዕለት የተሞከረውንና የከሸፈውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ያወገዘ ሲሆን ለሱዳን ውስጣዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ችግር እንዲያስከትል ተብሎ የተደረገ መሆኑ ድርጊቱን ማን እንደፈጸመው የሚያጣራ ቡድን እንዲቋቋምም ውሳኔ ተላልፏል፡፡በተያያዘ ዜና የግብጽ ከፍተኛ ባለሥልጣን ወደ ሱዳን ማቅናታቸው ተሰምቷል፡፡
ካርቱም የገቡት የግብጽ ደህንነት ዋና ዳይሬክተር አባስ ካማል ሲሆኑ ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀ መንበርና ከምክትላቸው ሌትናንት ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ጋር መወያየታቸው ተሰምቷል፡፡
የደህንነት ኃላፊው ወደ ሱዳ ያቀኑት የግድያ ሙከራው ከከሸፈ ከሰዓታት በኃላ ነው ተብሏል፡፡