በሀምዶክ ላይ ከተደረገው የግድያ ሙከራ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሱዳኑ አቻቸው ጋር በስልክ ተወያዩ
በሀምዶክ ላይ ከተደረገው የግድያ ሙከራ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሱዳኑ አቻቸው ጋር በስልክ ተወያዩ
ዛሬ ጠዋት በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ መወያየታቸው ተሰምቷል፡፡ የግድያ ሙከራው የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስራ ቦታ ታጅበው በሚሄዱበት መንገድ ላይ መሆኑን ነው ባለቤታቸው ሙና አብደላ በትዊተር ገፃቸው ይፋ ያደረጉት፡፡
ከግድያ ሙከራው በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በሙሉ ጤንነት ላይ መሆናቸውን በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ያስታወቁ ሲሆን ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋርም በስልክ ተነጋግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ የተፈጸመባቸውን የግድያ ሙከራ “የሽብር ድርጊት” ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ከግድያ ሙከራው በኋላ ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በስልክ መነጋገራቸውን የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ዳይሬክትር አሊ ባክሂት ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡ የአብደላ ሀምዶክን ጤንነት ለማወቅ ስልክ የደወሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ድርጊቱ ሱዳን የጀመረችውን የለውጥ ሂደት ማስቆም አይችልም ብለዋል፡፡
“በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ላይ ዛሬ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ አወግዛለሁ። የሱዳን ሕዝብ ሰላሙን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ የሚደነቅ ርምጃ ወስዷል። እንዲህ ያሉ ክሥተቶች የሱዳንን መረጋጋትና የለውጥ ጉዞ ሊያደናቅፉ አይገባም።” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌስ ቡክ ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ሱዳናውያን በጠቅላይ ሚኒስትራቸው ላይ የተሞከረውን የግድያ ሙከራ በማውገዝ በካርቱም አደባባይ ወጥተዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታትም /ኢጋድ/ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ አውግዟል፡፡ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር ) በሰጡት መግለጫ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ የሚወገዝ ነው ብለዋል፡፡ ሁሉም ሱዳናዊያን በሀገራቸው የተጀመረውን አካታች የፖለቲካ ውይይት እና ክርክር በማጠናከር ዘላቂ መረጋጋት፣ ሰላም እና ብልፅግና ለማረጋገጥ በጋራ እንዲሰሩም ኢጋድ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ድርጊቱን ያወገዘው የአሜሪካ መንግስትም ለሱዳን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ለሱዳን መንግሥትና ሕዝብ አስተማማኝ ሰላም እና ደህንነት እንዲሰፍን የጀመሩትን ጉዞ ከግብ እንዲያደርሱ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና የቁሳቁስ ድጋፍ መስጠቱን እንዲያጠናክርም ኢጋድ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ግድያው የተሞከረው መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ ሲሆን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መስሪያ ቤት ቅርብ ቦታ በሚገኘው ኮፐር በተባለ ድልድይ ላይ ነው፡፡
የግድያ ሙከራውን በተመለከተ ፖሊስ ምርመራ መጀመሩም ተገልጿል፡፡
አብዳለ ሀምዶክ ሱዳንን 30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሲያስተዳድሩ የነበሩት ኦማር ሀሰን አልበሽር በህዝባዊ ተቃውሞ እ.ኤ.አ. ሚያዚያ 2019 ከስልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡