የውጭ ሀገር ዜጎች ከሱዳን ከወጡ በኋላ ሁለቱ ወገኖች ወሳኝ ውጊያ ለማካሄድ ፍላጎት አላቸው ተብሏል
የሱዳን ጦር በካርቱም የሚገኘውን የፈጥኖ ደራሽ ሰፈር በአየር ደበደበ፡፡
13ተኛ ቀኑን በደፈነው የሱዳን ግጭት በጦር አውሮፕላኖች ከፍተኛ ጥቃት ተካሂዷል ተብሏል።
በሰሜናዊ ካርቱም በሚገኘው "ካፉሪ" የጦር አውሮፕላኖች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ኢላማዎች መደብደባቸው ተነግሯል።
በጦር ሰፈሩ አካባቢ በከባድ የጦር መሳሪያዎች የተደገፈ ጦርነት ተቀስቅሷል።
የጦር አውሮፕላኖቹ ከናይል ወንዝ በስተምስራቅ በሚገኘው “አል-ናስር” የሚገኘውን የፈጥኖ ደራሹ የጦር ሰፈር ላይም የቦምብ ጥቃት ፈጽሟል።
በካርቱም ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግስት አካባቢ ሁለቱ ወገኖች አልፎ አልፎ የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል የተባለ ሲሆን፤ ወደ መሀል ካርቱም መግባት አስቸጋሪ መሆኑ ቀጥሏልም ተብሏል።
“የሱዳንን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ”- ጄነራል ዳጋሎ
ጦሩ በሰጠው መግለጫ በመጪዎቹ ቀናት "በመሬት ላይ ትልቅ ለውጥ" እንደሚታይ ተናግሯል።
ጦሩ አክሎም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ በማዕከላዊ ካርቱም ወታደራዊ ካምፕ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሞክሯል ሲል ከሷል።
ኢጋድ የሱዳንን ጦርነት ለማስቆም ባቀረበው ተነሳሽነት ላይ የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አቋም ተለያይቷል ተብሏል።
በመርህ ደረጃ በጦር ኃይሎች አዛዥ ጀነራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሃን የጸደቀው ይህ ተነሳሽነት፤ ዛሬ ሀሙስ የሚያጠናቀቀውን አራተኛውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማራዘም እና የሁለቱን ወገን ተወካዮችን ወደ ጁባ መላክን የሚያካትት ነው።
ከሀገሪቱ የውጭ ሀገር ዜጎችን የማስወጣት ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለቱ ወገኖች ወሳኝ የሆነ ውጊያ ለማካሄድ ያላቸውን ፍላጎት ታዛቢዎች አስጠንቅቀዋል።