“ሱዳን ከጦርነቱ የበለጠ ጥንካሬና አንድነት ኖሯት ትወጣለች"- ሌ/ጄነራል አልቡርሃን
አል-ቡርሃን በኢድ አል-ፈጥር በዓል መልእክታቸው የሱዳን ህዝብ በአንድነት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል
አል ቡርሃን በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ስለታወጀው የ72 ሰዓት የተኩስ አቁም ያሉት ነገር የለም
“ሱዳን አሀን ከገባችበት ጦርነት የበለጠ ጠንካሬና አንድነት ኖሯት ትወጣለች” አሉ የሱዳን ጦር መሪ ሌ/ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን።
ሌ/ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ዛሬ እየተከበረ ያለውን የኢድ አል ፈጥር በዓል አስመልክተው ጠዋት ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
አልቡርሃን በኢድ አል-ፈጥር በዓል መልእክታቸው የሱዳን ህዝብ በአንድነት እንዲቆም ጥሪ ያስተላለፉ ሲሆን፤ ሀገሪቱ አሁን ከገባችበት ቀውስ በጥበብ እና በኃይል እንደምትወጣው እምነት አለኝ ብለዋል።
ሱዳን አሁን ከገባችበት ጦርነትም የበለጠ አንድነት እና ጥንካሬን ይዛ እንደምትወጣም ሌ/ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እምነታቸውን ገልጸዋል።
ይህም ሀገሪቱን እና የሀገሪቱን ህዝቦች ለመጠበቅ እንዲሁም ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንዲከናወን የሚያስችል ይሆናል ሲሉም ተናረዋል።
ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤ.ኤፍ) ተብሎ በሚጠራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል የኢድ አልፈጥር በዓልን በማስመልከት ለ72 ሰዓት የሚፀና ተኩስ አቁም ማወጁ ይታወቃል።
ሆኖም ግን የሱዳን ጦር መሪ ሌ/ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ስለታወጀው ተኩስ አቁም ላይ አስተያየት አልሰጡም ነው የተባለው።
ዛሬ ጠዋት ላይ በካርቱም የተኩስ ድምጾች የተሰሙ ሲሆን፤ ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤ.ኤፍ) ተብሎ በሚጠራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሱዳን ጦር ተኩስ ከፍቶብኛል ብሎ ከሷል።
በሱዳን ጦር እና ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤ.ኤፍ) ተብሎ በሚጠራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ባሳለፍነው ቅዳሜ የተጀመረው ጦርነት ሳምንቱን ሙሉ ቀጥሎ ሲካሄድ ቆይቷል።
በካርቱም በተጀመረው እና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በተስፋፋው ጦርነት ከ320 በላይ ሰዎች መሞታቸው የተነገረ ሲሆን፤ ከ3 ሺህ 200 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው መረጃዎች የተጠቁማሉ።
ከሞቱ ሰዎች መካከል የአሜሪካ ዜጋ እንደሚገኝበት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በጦርነቱ ዜጎቿ እንደሞቱባት ማሳወቋ ይታወሳል።