የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አብዱለፈታህ አልቡርሀን ዛሬ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ንግግር ያደርጋሉ
በሱዳን ጦርነት መጀመርያ ዋና ከተማዋን ካርቱም በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የተነጠቀው የሱዳን ጦር ዋና ከተማዋን ድጋሚ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ውግያ መክፈቱ ተሰምቷል፡፡
17 ወራትን ያስቆጠረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በድርድር ለመቋጨት የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም እስካሁን ስኬታማ መሆን አልቻሉም፡፡
የሀገሪቱን ሰፊ ክፍል ተቆጣጥሮ የሚገኝው በጄነራል ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራው ሀይል በጦሩ የተከፈተበትን ውግያ ለመከላከል ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
የውግያ ጄቶችን እና ታንኮችን አካቷል የተባለው ዛሬ ከንጋቱ አንስቶ የተጀመረው ውግያ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ካምፕ ናቸው በተባሉ ስፍራዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡
በካርቱም ፣ ኦምዱርማን እና ባሃሪ አካባቢዎች በአሁኑ ሰአት የሁለቱ ጄነራሎች ጦር በመዋጋት ላይ ይገኛል፡፡
የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ በበኩሉ በቅርብ ወራት የተለያዩ የሱዳን ክፍሎችን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ግስጋሴ መቀጠሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከዚህ ባለፈም የሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ የሆነችውን አልፋሺር ለመቆጣጠር እየተደረገ በሚገኝው ውግያ የሀምዳን ዳጋሎ ጦር ከተማዋን በመክበብ ከፍተኛ ጥቃት እያደረሰ እንደሚገኝ ነው የተነገረው፡፡
አልፋሺር በዳርፉር ክልል የሀገሪቱ ጦር ጠንካራ ይዞታ የሚገኝባት የመጨረሻዋ ስፍራ እንደሆነች መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
የተባበሩት መንገስታት ድርጅት በዚህ አካባቢ በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው የሰበአዊ መብት ጥሰት መበራከቱን ሲገልጽ አስገድዶ መድፈር ፣ የወሲብ ባርነት ፣ እገታ እና ህጻናትን ለወታደርነት መመልመል እየተስፋፋ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ከጠቅላላ ህዝቧ ግማሽ ያህሉ ተፈናቃይ በሆነባት ሱዳን ከጦርነቱ በተጨማሪ ርሀብ እና ተላላፊ በሽታዎች የዜጎችን ህይወት በስቃይ የተሞላ እንዳደረጉት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስፋፋ በሚገኝው የኮሌራ በሽታ ብቻ እስካሁን ከ450 በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡
መድሀኒት እና አስቸኳይ ሰበአዊ እርዳታዎችን በበቂ ሁኔታ ማሰራጨት ካልተቻለም በርሀብ እና በሽታ የሚሞቱ ሰዎች በጦርነቱ ከሚሞቱት ሊልቅ እንደሚችል ተመድ አስጠንቅቋል፡፡