የጀነራል ሄሜቲ ጦር ከካርቱም በስተደቡብ ምስራቅ የምትገኘውን ወሳኝ ከተማ ተቆጣጠረ
የዋድ መዳኒ መያዝ በምዕራብ እና በማዕከላዊ ሱዳን እያጠቁ ላሉት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ወሳኝ ምዕራፍ ነው ተብሏል
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ከካርቱም በስተደቡብ ምስራቅ በኩል ወደምትገኘው ከተማ መጠጋት ከጀመሩበት ከባለፈው አርብ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሸሽተዋል
በጀነራል ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ የሚመሩት የሱዳን ፈጥኖ ደረሽ ኃይሎች ከካርቱም በስተደቡብ ምስራቅ የምትገኘውን ዋድ መዳኒ ከተማን ተቆጣጠሩ።
ከሱዳን ጦር ጋር ግጭት ውስጥ የገቡት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በተፈናቃዮች ወደ ተጨናነቀችው እና የእርዳታ ማዕከል ወደ ሆነችው ዋድ መዳኒ ከተማ መግባታቸውን ሮይተርስ እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ዋድ መዳኒ ከተማን መያዛቸው በምዕራብ እና በማዕከላዊ ሱዳን እያጠቁ ላሉት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ወሳኝ ምዕራፍ ነው ተብሏል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ከካርቱም በስተደቡብ ምስራቅ በኩል ወደምትገኘው ከተማ መጠጋት ከጀመሩበት ከባለፈው አርብ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሸሽተዋል።
ዋድ መዳኒ በግብርና ምርት የምትታወቀው የአል ገዚራ ግዛት ዋና ከተማ ነች።
ዋድ መዳኒ ከካርቱም ግጭቱን ሸሸተው ለመጡ ከ85ሺ በላይ ተፈናቃዮች የጤና፣ የምግብ እና የመጠለያ አገልግሎት ስትሰጥ ቆይታለች።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ወደ ከተማ ገብተዋል ስለተባለው ጉዳይ የሱዳን ጦር ያለው ነገር የለም።
ጦርነት የገጠሙት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና የሱዳን ጦር የቀድሞ ፕሬዝዳንት አልበሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ከተመሰረተው የሲቪል የሽግግር መንግስት ጋር ስልጣን ተጋርተው መርተዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በለቀቁት ቪዲዮ በጭነት መኪና ጥቅጥቅ ብለው የተጫኑ ወታደሮች በዋድ መዳኒ ከተማ ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል።
የካቶሊክ ቄሶችም መሳሪያ በእጁ የያዘ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ታጣቂን ከተማዋን ለቆ ለመሄድ እርዳታ ሲጠይቁት ይታያሉ።
ስምንት ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ተገድለዋል፣ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ሮይተርስ የቪዲዮን ትክክለኛነት ማረጋገጥ እንደማይችል ገልጿል።
አሜሪካ የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ውሳኔ ላይ ደርሳለች።