በሱዳን መዲና ካርቱም አባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ መፍረሱ ተገለጸ
የካርቱም ውበት አንድ አካል የነበረው ይህ ድልድይ የፈረሰው በከባድ መሳሪያ ተመቶ ነው ተብሏል
የሱዳን ብሔራዊ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ለድልድዩ መመታት እርስ በርስ ተካሰዋል
በሱዳን መዲና ካርቱም አባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ መፍረሱ ተገለጸ።
በጎረቤት ሀገር ሱዳን በብሔርራዊ ጦሩ እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች መካከል ጦርነት ከተጀመረ ሰባተኛ ወሩ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች ካሳለፍነው ሚያዝያ ወር ጀምሮ እየተዋጉ ሲሆን በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ሲገደሉ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሱዳናዊያን ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።
እልባት ባልተገኘለት በዚህ ጦርነት በሀገሪቱ መዲና በአባይ (ናይል) ወንዝ ላይ በተገነባው ድልድይ ላይ በተፈጸመ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ምክንያት ድልድዩ መፍረሱ ተገልጿል።
የሀገሪቱ ዋና ከተማ ካርቱምን ከኦምዱርማን የሚያገናኘው ይህ ድልድይ ሻምባት የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን አገልግሎት መስጠት በማይችልበት ሁኔታ መውደሙን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ድልድዩን ማን መታው? የሚለው ጉዳይ እስካሁን ግልጽ ያልሆነ ሲሆን አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጣት ከመጠቋቆማቸው ባለፈ ሀላፊነት የወሰደ አካል የለም ተብሏል።
ይህ በዚህ እንዳለም በዳርፉር ግዛት በአንድ ቀን አንድ ሺህ ገደማ ሱዳናዊያን ተገድለዋል የተባለ ሲሆን ግድያውን በጀነራል ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች እንደፈጸሙት የሀገሪቱ ብሔራዊ ጦር አስታውቋል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል የቀረበበትን ክስ ውድቅ ያደረገ ሲሆን አብዛኞቹን የሱዳን አካባቢዎች በመቆጣጠር ላይ መሆኑን ገልጿል።
ከአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጋር እየተዋጋ ያለው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መላውን የሱዳን አካባቢዎች እቆጣጠራለሁም ብሏል።
የፈጥኖ ደራሹ ምክትል ኮማንደር የሆኑት አብዱልራሂም ሐምዳን ዳጋሎ ኃይላቸው ወደፊት የሚያደርገውን ግስጋሴ አስቀጥሎ ሁሉንም የሱዳን ግዛቶች በቁጥጥሩ ስር ያስገባል ብለዋል።
የቡድኑ ምክትል ኮማንደር ይህን ያሉት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የአገሪቱን ጦር ኃይል ከሱዳን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ማስወጣቱ ከተገለጸ ከቀናት በኋላ ነው።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሠራዊት ከወራት ውጊያ በኋላ የአገሪቱን ጦር በማስወጣት የደቡብ ዳርፉር ዋና መዲና የሆነችውን ኛላ ከተማ ይዘዋል።
ምክትል ኮማንደር አብዱልራሂም ሐምዳን ዳጋሎ በማዕከላዊ ዳርፉር ግዛት ከድል በኋላ ደስታቸውን እየገለጹ ለነበሩ ወታደሮች ንግግር ሲያደርጉ፤ “ወደ ተቀሩት ግዛቶች እና የጦሩ ዋና መቀመጫዎች እንዘምታለን፤ ፈጣሪ ከፈቀደ በቁጥጥራችን ስር እናስገባቸዋለን” ብለዋል።
የጀነራል ሃምዳን ደጋሎ ወንድም እንደሆኑ የሚገለጸው የፈጥኖ ደራሹ ምክትል መሪ አብዱልራሂም ዳጋሎ ኛላ ከተማን ለመያዝ የተደረገውን ኦፕሬሽን መምራታቸው ተገልጿል።