የሱዳኑ ጀነራል ሄሜቲ ጦር በረመዳን ተኩስ እንዲያቆም የቀረበለትን ጥሪ ተቀበለ
የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ ከሆነ 11 ወራት ያስቆጠሰውን ጦርነት ጋብ ያደርገዋል
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በረመዳን ወር ተኩስ እንዲያቆም በተመድ የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሏል
የሱዳኑ ጀነራል ሄሜቲ ጦር በረመዳን ተኩስ እንዲያቆም የቀረበለትን ጥሪ ተቀበለ።
በጀነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በእስልምና እመት ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ተደርጎ በሚወሰደው የረመዳን ወር ተኩስ እንዲያቆም በተመድ የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሏል።
የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ ከሆነ 11 ወራት ያስቆጠሰውን ጦርነት ጋብ ያደርገዋል።
የረመዳን ፆም በነው እለት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ባወጣው መግለጫ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ በችግር ውስጥ ያሉት ሱዳናውያን እርዳታ እንዲያገኙ እና ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በር የሚከፍት ነው ብሏል።
በጀነራል ሄሜቲ በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና በጄነራል አል ቡርሃን በሚመራው የሱዳን ጦር መካከል ጦርነት የተጀመረው በሚያዝያ 2023 ነበር።
ተመድ 25 ሚሊዮን የሚሆነው ወይም ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሱዳን ህዝብ እርዳታ እንደሚፈልግ እና ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልጿል።
አሜሪካ ሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሳለች።
ይህን ደም አፋሳሽ ጦርነት በድርድር ለማስቆም አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ የሁለቱን ተወካዮች ማደራደር ጀምረው የነበረ ቢሆንም ያለውጤት ተቋርጧል።
ተፋላሚዎቹ በድርድር ግጭቱን ለመፍታት የተቸገሩት ሁለቱም እናሸንፋለን የሚል ግምት በመውሰዳቸው እንደሆነ ዲፕሎማቶች ይናገራሉ።