የሱዳን ጦር እስካሁን ከ100 በላይ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ተኩሶ ገድሏል ተብሏል
በሱዳን ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱ ተገለፀ።
በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በሚመራው የሀገሪቱ ሲቪል አስተዳድር ላይ ከስድስት ወር በፊት መፈንቅለ መንግስት መፈጸሙ ይታወሳል።
ስልጣን የተቆጣጠረው የሱዳን ጦርም የሲቪል አስተዳድሩን ከስልጣን በማገድ የራሱን ወታደራዊ መንግስት ማቋቋሙን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል።
ሱዳናዊያንም የሀገሪቱ ጦር ስልጣን ለሲቪል አስተዳድር እንዲያስረክብ ሀገር አቀፍ ተቃውሞዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
ሱዳናዊያን አሁንም ተቃውሟቸውን በተለያዩ መንገዶች የቀጠሉ ሲሆን፤ በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ወታደራዊ መንግስትም ጥሎት የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከስድስት ወራት በኋላ ማንሳቱን ገልጿል።
ወታደራዊ የሽግግር ጊዜ አስተዳድር እንዳሳወቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳው በሀገሪቱ ለተጀመረው ብሄራዊ ውይይት መደላድል ለመፍጠር በማሰብ ነው ብሏል።
ሱዳናዊያን በሀገሪቱ ወታደራዊ መንግስት ላይ ተቃውሟቸውን የቀጠሉ ሲሆን የሱዳን የጸጥታ ሀይሎች እስካሁን ከ100 በላይ ተቃዋሚ ዜጎችን ተኩሰው ገድለዋል ተብሏል።
የሀገሪቱ የጸጥታ ሀይሎች ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ተቃዋሚዎችን እና መሪዎችን እንዳሰረ የተገለጸ ሲሆን የታሰሩት እንዲፈቱ ተመድን ጨምሮ በርካቶች በማሳሰብ ላይ ናቸው።