ሱዳን ከእስራኤል ጋር ምንም ግንኙነት እንዳይኖራት ያወጣችውን ሕግ ሰረዘች
በ 1958 የወጣው ሕጉ ሱዳን ከእስራኤል ጋር ምንም አይነት የዲፕሎማሲ እና የንግድ ግንኙነት እንዳይኖራት ያግዳል
በሽግግር መንግስቱ የተሰረዘው ሕግ በፓርላማው ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚሆን ይጠበቃል
የሱዳን ካቢኔው ዛሬ ማክሰኞ ባካሄደው ስብሰባ ሀገሪቱ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዳይኖራት የሚያግደው ሕግ እንዲሰረዝ የወጣውን ረቂቅ አፀደቀ፡፡
በሕጉ የመሰረዝ ጉዳይ ላይ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ልዩነት ቢኖርም ፣ በስተመጨረሻ እንዲፀድቅ ተደርጓል ነው የተባለው፡፡
የሽግግሩ ጊዜን በሚገዛው ህገ-መንግስታዊ ሰነድ መሰረት በሉዓላዊ የሽግግር መንግስቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና በፓርላማው የጋራ ስብሰባ ፣ ረቂቁ ሕግ ሆኖ ወደ ትግበራ እንዲገባ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እስራኤል የሱዳንን ውሳኔ በማድነቅ መግለጫ አውጥታለች፡፡ ውሳኔው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚረዳ ነው እስራኤል ያስታወቀችው፡፡
ሱዳን እና እስራኤል እንደ አውሮፓውያኑ ጥቅምት 23 የሰላም ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን ይህን እርምጃ በመውሰድ ሱዳን አምስተኛዋ የአረብ ሀገር ነች፡፡
ሱዳን ከእስራኤል ጋር ግንኙነት እንዳይኖራት የሚከለክለው ፣ እ.ኤ.አ በ 1958 የወጣው ሕግ ፣ ከእስራኤል የተገዙ እና የሀገሪቱ ምርት የሆኑ ምንም ዓይነት ሸቀጣ ሸቀጦች ወደ ሱዳን እንዳይገቡ እና በሱዳን ለገበያ እንዳይቀርቡ ያግዳል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል ማናቸውንም የንግድ ትብብርም የሚከለክለውን ይህን የሱዳን ሕግ የጣሰ ማንኛውም አካል እንደሚቀጣም ተደንግጎ ነበር፡፡ ሕጉን የጣሱ እስከ 10 ዓመት እስራት እና ከባድ የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡