የኬንያው ፕሬዝዳንት የሱዳን ጄነራሎች “ይህን የማይረባ ጦርነት ሊያቆሙ ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ
ፕሬዝዳንት ሩቶ የሱዳን ጄኔራሎች በአፍሪካ ገንዘብ በተገዙ መሳሪያዎች ሀገሪቱን እያወደሙ ነው ብለዋል
“በሱዳን ያለውን ጦርነት ማስቆም አቅም አላገኘንም” ሲሉም ፕሬዝዳንት ሩቶ የአፍሪካ ሀገራትን ተችተዋል
የኬንያው ፕሬዝዳት ዊሊያም ሩቶ በውጊያ ላይ ያሉ ሁለቱ የሱዳን ጄነራሎች በአስቸኳይ ጦርነት ሊያቆሙ ይገባል ሲሉ በድጋሚ ጥሪ አቀረቡ።
በሱዳን ጦር እና አር.ኤስ.ኤፍ ተብሎ በሚጠራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት አንድ ወር አልፎታል።
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱምን ጨምሮ የካርቱም ጎረቤቶች በሆኑት ባህሪ እና ኦምዱርማን ከተሞች ላይ አሁንም ከባድ ውጊያዎች ቀጥለው እየተካሄዱ መሆኑ ይታወቃል።
የኬንያው ፕሬዝዳት ዊሊያም ሩቶ በትናትናው እለት በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የፓን አፍሪካ ፓርላማ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር የሱዳን ጄነራሎች በአፍሪካ ገንዘብ የተገዙ የጦር መሳሪያዎችን በመጠቀም መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ ሆስፒታሎችን እና አውሮፕላን ማረፊያዎችን እያወደሙ ነው ብለዋል።
“ለሁለቱ የሱዳን ጦር ጄነራሎች ይህንን የማይረባ ጦርነት እንዲያቆሙ ልንነግራቸው ይገባል” ሲሉም ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንት ሩቶ አክለውም የአንድ ሀገር ጦር ሰራዊት ስራው ሽብርተኞችን እና ወንጀለኞችን መዋጋት እንጂ ህጻናት እና ሴቶችን መውጋት አይደለም ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ ሀገራትንም የተቹ ሲሆን፤ የሱዳንን ጦርነት ማስቆም ባለመቻላችን የራሳችን ሰላምና ደህንነት በሌሎች ገንዘብ ድጋፍ አድራጊነት እየተሰጠን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በሚመራው የሱዳን ጦርና በጄነራል ሀምዳን ዳጋሎ በሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከተጀመረ አንድ ወር አስቆጥሯል።
በሱዳን ጦርነት እስካሁን 1 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ሞተዋል የተባለ ሲሆን፤ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውም ነው ዘገባዎች የሚያመላክቱት።
ከተፈናቃዮች መካከልም 200 ሺህ ያህል ሱዳናውያን ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ሲሆን፤ በካርቱም የሚገኙ ሰዎችም ለህይወታቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም ነው የተገለጸው።