ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን ኤል ገዳሬፍ መተላለፊያ መዝጋቷ ተሰማ
በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በመተማ ከባድ ውጊያ ሲደረግ መሰንበቱ ተገልጿል
በመተማ የሚገኙ የሱዳን ስደተኞች ውጊያው የውሃ እና ምግብ አቅርቦትን ማወኩን ተናግረዋል
ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን የኤል ገዳሬፍ የድንበር መተላለፊያ ከትናንት ማለዳ ጀምሮ መዝጋቷ ተነገረ።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) የሚያስተዳድረው ሪሊፍዌብ ድረገጽ እንዳስነበበው ካርቱም መተላለፊያውን የዘጋችው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች ውጊያ አሳሳቢ ነው በሚል ነው።
በመተማ የሚገኙ የሱዳን ስደተኞች የፋኖ ታጣቂዎች ከተማዋን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ለሱዳኑ ራዲዮ ዳባንጋ መናገራቸውንም ነው ድረገጹ የጠቆመው።
በከተማዋ ለቀናት የተካሄደው ከባድ ውጊያ ሱቆች እንዲዘጉና የውሃ እና ምግብ አቅርቦትን ለሁለት ቀናት እንዲቋረጥ ማድረጉን ስደተኞቹ ለሬዲዮ ጣቢያው ገልጸዋል።
የጸጥታ ሁኔታው የረድኤት ድርጅቶችም የመጠጥ ውሃ እና ምግብ ለማቅረብ እንዳይችሉ እንቅፋት መሆኑ ነው የተነገረው።
የሱዳን ኤል ገዳሬፍ ግዛት አስተዳደር 2 ሺህ 716 ሱዳናውያን ስደተኞች ወደ ሱዳን ተመልሰው በኤል ጋላባት ከተማ በሚገኝ መጠለያ ካምፕ እንዲሰፍሩ መደረጉን እሁድ ነሃሴ 26 2016 አስታውቆ ነበር።
የግዛቷ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ሌተናል ጄነራል ሞሃመድ አህመድ ሃሰን የደህንነት ስጋት አለብን ያሉት ሱዳናውያን ስደተኞች በፈቃዳቸው በተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና በኖርዌይ የስደተኞች ምክርቤት ትብብር ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን አንስተዋል ይላል የሪሊፍዌብ ድረገጽ።
የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ (አርኤስኤፍ) ባለፈው አመት ውጊያ መጀመራቸውን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
ጦርነትን ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ (አማራ ክልል) የገቡት ሱዳናውያን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች ውጊያ እና የሽፍታዎች ጥቃት ፈተናቸውን እንዳበዛባቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
በቅርቡም አውላላ ከተባለው የስደተኞች ጣቢያ 2 ሺህ 500 ሱዳናውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው የሚታወስ ነው።
የኤል ገዳሬፍ አስተዳደር ከኢትዮጵያ የሚመለሱትን ሱዳናውያን ስደተኞች በድንበር ከተማዋ ኤል ጋላባት ሶስት ካምፖችን በማቋቋም ለመቀበል ከመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር ስምምነት ላይ መድረሱም በዘገባው ለትውስታ ተነስቷል።
የሱዳኑ ሬዲዮ ዳባንጋ እና የኦቻው ሪሊፍዌብ ድረገጽ ላስነበቡት የኤል ገዳሬፍ መተላለፊያ መዘጋት ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።