ሱዳን የግብጽ እና የአሜሪካ አደራዳሪዎችን ለማግኘት የልኡክ ቡድን ወደ ካይሮ ልትልክ ነው
የሱዳን መንግስት በሳኡዲ አረቢያ ጂዳ የተደረሰው ስምምነት ካልተፈጸመ በስዊዘርላንድ በሚካሄደው የሰላም ስብሰባ እንደማይሳተፍ ገልጿል
ሀሰን አል በሽር በህዝባዊ አመጽ ከተወገዱ በኋላ ስልጣን በያዙት ጀነራሎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ሀገሪቱን ቀውስ ውስጥ ከቷታል
ከግብጽ እና ከአሜሪካ አደራዳሪዎች ጋር ለመወያየት ወደ ካይሮ የልኡክ ቡድን እንደሚልክ የሱዳን መንግስት በዛሬው እለት አስታወቀ።
በጦሩ ቁጥጥር ስር ያለው እና ሀገሪቱን ለመቆጣጠር ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጋር እየተዋጋ መንግስት፣ከዚህ በፊት በሳኡዲ አረቢያ ጂዳ የተደረሰው ስምምነት ካልተፈጸመ በስዊዘርላንድ በሚካሄደው የሰላም ስብሰባ እንደማይሳተፍ ገልጿል።
በአሜሪካ የሚመራው እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር የሚሳተፍበት ይህ ስብሰባ በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2023 የተጀመረውን እና 50 ሚሊዮን ከሚሆነው የሱዳን ህዝብ ግማሽ ያህሉ ለምግብ እጥረት እንዲዳረግ ምክንያት የሆነው ጦርነት እንዲቆም የማድረግ አላማ አለው።
በሱዳን ጦር መሪ የሚመራው የሽግግር ሉአላዊ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ወደ ካይሮ የልኡክ ቡድን ለመላክ የወሰነው ከአሜሪካ ተወካይ እና ከግብጽ መንግስት ጋር ከተወያየ በኋላ ነው ብሏል።
በጂዳ የተፈረመው እና የሱዳን ጦር ንግግር ለማድረግ እንደቅደመ ሁኔታ ያስቀመጠው፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ከሲቪሊያን ቀጣና እንዲወጡ ተደርሶ የነበረውን ስምምነት ነው።
የሱዳን መንግስት የራሱን ፍላጎት ለአሜሪካ እና ለሳኡዲ አረቢያ አደራዳሪዎች ማሳወቁን ሮይተርስ ከፍተኛ የመንግስት ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የሱዳን መንግስት ወደ ጄኔቫ ስዊትዘርላንድ የልኡክ ቡድን ልኳል የሚለውን የሚዲያ ሪፖርት ምንጩ ማስተባበሉን ዘገባው ጠቅሷል።ሱዳን ለሶስት አስርት አመታት ሲያስተዳድሩ የነበሩት ሀሰን አል በሽር በህዝባዊ አመጽ ከተወገዱ በኋላ ስልጣን በያዙት ጀነራሎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ሀገሪቱን ቀውስ ውስጥ ከቷታል።
በሀገሪቱ ወደ ሲቪል አስተዳደር ትሸጋገራለች የሚለው ውጥንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግስት በመፈጸሙ ከሽፏል።
አንድ አመት ከአራት ወራት በላይ ጊዜ ያስቆጠረው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ እና ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓቸዋል።