ሱዳን በመተማ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኛትን መንገድ ከፈተች
ሱዳን ድንበሩን የከፈተችው የሀገሪቱ የጸጥታ እና መከላከያ ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ተከትሎ ነው
ውሳኔው በሀገራቱ መካከል ለተቀሰቀሰው ውጥረት“አፋጣኝ እና ዘላቂ”መፍትሔ ለማበጀት ያለመ ነው ተብሏል
በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ ሁለቱም ሀገራት የሚያዋስነውና በገላባት እና መተማ መካከል የሚገኘው የኢትዮጵያ እና የሱዳን የድንበር ኬላ ለአንድ ወር ያክል ዝግ ሆኖ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡
ድንበሩ ከትናንት እሁድ እለት ጀምሮ ክፍት ማድረጓንም ነው ሱዳን ያስታወቀቸው፡፡
ሱዳን ድንበሩን ክፍት ያደረገቸው በጄነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የሱዳን የጸጥታ እና መከላከያ ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ተከትሎ ነው፡፡
- ኢትዮጵያ “የሱዳን ወታደሮች የተገደሉት ወደ ድንበሬ ዘልቀው በመግባታቸው ነው” አለች
- ሱዳን በኢትዮጵያ የተገደሉባትን ወታደሮች አስመልክታ “ለፀጥታው ምክር ቤት ላመለክት ነው” አለች
ውሳኔው የሁለቱ ሀገራት አመራሮች በድንበር አካባቢ ለተቀሰቀሰው ውጥረት “አፋጣኝ እና ዘላቂ” መፍትሔ ለማበጀት የጀመሩትን ውይይት መነሻ በማድረግ እንዲሁም “የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሱዳን ግዛት ሰርገው እንዳይገቡ ለመከላከል ከኢትዮጵያ በኩል ለታየው መልካም ፈቃድ” የተላለፈ ምላሽ መሆኑን ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
መግለጫው “እውቅና ባለው ህጋዊ አሰራር መሰረት የገላባት ድንበር ማቋረጫ በሁለቱ ሀገራት መካከል እንቅስቃሴ እንዲኖር በሚል ከዛሬ ሰኔ 17 ጀምሮ እንዲከፈት ተወስኗል” ብሏል።
"በሁለቱ ሀገራት መካከል ጥብቅ ቅንጅት በማድረግ የዓለም አቀፍ የድንበር ቁጥጥር እንዲጠናከር እና የትኛውም የታጠቁ ሃይሎች በሁለቱ ሀገራት መካከል እንዳይንቀሳቀሱ ተወስኗል" ሲልም አክሏል መግለጫው፡፡
በድንበር አካባቢ 6 የሱዳን ወታደሮች መገደላቸውን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል ውጥረት በመንገሱ ምክንያት ገላባት ኬላ ከሰኔ 27 ቀን 2022 ጀምሮ ዝግ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳን ወታደሮች ድንበር ጥሰው መግባታቸውን እና ትንኮሳ መፈጸማቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡
በቅረቡ በናይሮቢው የኢጋድ አባል ሀገራት የተገናኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሱዳኑ መሪ አል ቡርሃን ለዘመናት የዘለቀውን ጉርብትናንና ወዳጅነትን በማስቀደም የተፈጠረው ውጥረት በውይይት ለመፍታት በሚቻልባቸው መፍትሄዎች ዙሪያ መምከራቸውም የሚታወስ ነው፡፡