ሱዳን፤ አቶ ደመቀ ከሰሞኑ ለምክር ቤት የሰጡትን ማብራሪያ አወገዘች
አቶ ደመቀ በሱዳን የተወሰደ የኢትዮጵያ ግዛት መኖሩን ጠቅሰው "በየትኛውም መመዘኛ ይመለሳል" ሲሉ በምክር ቤት መናገራቸው ይታወሳል
ተወስደዋል ያሏቸውን የኢትዮጵያ ግዛቶች በተመለከተ ያደረጉት ንግግር የተሳሳተ እንደሆነ ሱዳን ገልጻለች
ሱዳን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሰሞኑ ተወስደዋል ያሏቸውን የኢትዮጵያ ግዛቶች በተመለከተ ለተወካዮች ምክር ቤት የሰጡትን ማብራሪያ አወገዘች፡፡
ካርቱም በአቶ ደመቀ የተሰጠው ማብራሪያ የተሳሳተ እና ከአሁን ቀደም የተደረጉ ስምምነቶችን የጣሰ ነው ብላለች፡፡
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማብራሪያውን አውግዞ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው አቶ ደመቀ "አል ፋሽቃ የተባለውን የሱዳን ግዛት" በተመለከተ የሰጡት ማብራሪያ በሃገራቱ ድንበር ምልክቶችን ለማስቀመጥ በ1902 የተደረገውን ስምምነት፣ የ1903ቱን ፕሮቶኮል እንዲሁም የሁለቱ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በ1972 ባደረጓቸው የማስታወሻ ልውውጦች ኢትዮጵያ የሰጠችውን እውቅና የሚጥስ ነው ብሏል፡፡
ማብራሪያው የጥላቻ ንግግሮችንና ውጥረትን በማርገብ ቀጣናውን ማረጋጋት በሚያስፈልግበት በዚህ ወቅት የተሰጠ መሆኑንም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡
ሱዳን የጸጥታ ኃይሎቿን በማሰማራት የራሷን ግዛትና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን የድንበር ይዞታዎቿን የመጠበቅና የመቆጣጠር ሉዓላዊ መብት እንዳላት ለማስገንዘብ እንወዳለንም ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የጠበቀ ወንድማዊ ቁርኝት በማስታወስም የድንበር ጉዳዮችን ለማጠናቀቅ በጋራ የተቋቋመው የድንበር ኮሚቴ በቶሎ ስራ የሚገባበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጠይቋል፡፡
ከሱዳን ጋር ለገጠማት የድንበር ችግር ድርድርና ንግግርን እንደምታስቀድም ከአሁን ቀደም ደጋግማ ስትገልጽ የነበረችው ኢትዮጵያ ጉዳዩ በተቋቋመው የጋራ ኮሚቴ በኩል እልባት እንደሚያገኝ መግለጿ ይታወሳል፡፡
ባሳለፍነው ሃሙስ ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ/ም ለምክር ቤት ባቀረቡት የ9 ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት ጉዳዩን ያነሱት አቶ ደመቀ መኮንንም ችግሩን ለመፍታት ኢትዮጵያ አሁንም ለሰላም አማራጮች በሯን ክፍ አድርጋ እየተጠባበቀች እንደሆነ በመጠቆም ይህ የማይን ከሆነ በሱዳን የተወሰደው የኢትዮጵያ ግዛት "በየትኛውም መመዘኛ" እንደሚመለስ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ሱዳን፤ ኢትዮጵያ በሰሜን የገጠማትን ችግር እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅማ ወረራ መፈጸሟን ያነሱት አቶ ደመቀ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ከመውረር ባለፈ የአካባቢውን ነዋሪዎች ማፈናቀሏንና የንብረት ውድመት ማድረሷን መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡