ሱዳን አል በሽርን ጨምሮ የዳርፉር ጅምላ ጭፍጨፋ ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ ለመስጠት ቁርጠኛ ነኝ አለች
ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የሱዳን ባለስልጣናት ተጠርጣሪዎቹን አሳልፎ ለመስጠት የሚያስችል ተግባራዊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጠይቋል
ካርቱም ተጠርጣሪዎቹን ወንጀለኞች ቶሎ አሳልፎ በመስጠት ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለመተባበር ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች
የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አል በሽርን ጨምሮ ሌሎችን የዳርፉር ጅምላ ጭፍጨፋ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኗን አስታወቀች፡፡
ካርቱም በዚህ ረገድ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን ለመተባበር ያላትን ዝግጁነት ለፍርድ ቤቱ ዋና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከሪም አሳድ ከሃን ገልጻለች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መርየም አል ሳዲቅ አል መህዲ ከዋና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከሪም አሳድ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አል በሽርን ጨምሮ ሌሎችን የዳርፉር ጅምላ ጭፍጨፋ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ ለመስጠት ሃገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን የገለጹት መርየም የሃገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህንኑ ለማድረግ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በተደረሰው ስምምነት መሰረት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ መንግስታቸው እንደሚሰራም ነው መርየም የተናገሩት፡፡
ዋና ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉን በጽህፈት ቤታቸው ያነጋገሩት የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት መሃመድ ሃምዳን ዳገሎ (ሄሜቲ)ም ሃገራቸው ፍርድ ቤቱን ለመተባበር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡
ዋና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከሪም በበኩላቸው የፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድን በቀጣዩ ወር ሱዳን እንደሚመጣ ገልጸው ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹን ለፍርድ የሚያቀርበው ባለስልጣናቱ በሚያደርጉት ትብብር ልክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፕሬዝዳንት አል በሽር አገዛዝ እ.ኤ.አ በ2003 በዳርፉር ተቀስቅሶ የነበረውን የአማጽያን እንቅስቃሴ ለማፈን በሚል በወሰደው እርምጃ 300 ሺ ገደማ ሰዎች መገደላቸውና 2.7 ሚሊዬን ሰዎች መፈላቀላቸው ይነገራል፡፡
ይህን ተከትሎ ፕሬዝዳንት በሽርን ጨምሮ በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አብደል ራሂም መሃመድ ሁሴን እንዲሁም የቀድሞው የሰሜናዊ ኮርዶፋን ግዛት ዋና አስተዳዳሪ አህመድ ሃሩን በዓለም አቀፍ ወንጀል ይፈለጋሉ፡፡