ሱዳን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሱዳንን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባታቸው ቅር መሰኘቷንም ገልጻለች
ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደሯን መጥራቷ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በትግራይ ክልል ያለውን ግጭት እንዲያበቃ ሱዳን የምታደርገውን ጥረት ሳይቀበሉት መቅረታቸውን አትቷል፡፡
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በትግራይ ጉዳይ የሱዳን የማደራደር ሚናን በተመለከተ ከሰሞኑ ሲሰጡት የነበሩት መግለጫዎች የሱዳን መንግስት ሲከታተለው ነበር ያለው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ ባለስልጣናቱ የሱዳን “ተዓማኒነት”ን ጥያቄ ውስጥ ማስገባታቸውና የኢትዮጵያ መሬት እንደተቆጣጠረች አድርግው ማቅረባቸው ሱዳን ቅር ተሰኝታለችም ብሏል፡፡
ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ በኩል እየቀረቡ ያሉ ክሶች “እንግዳ ናቸው”ም ነው ያለው፡፡
ሚኒስቴሩ ሱዳን በግጭቱ ውስጥ ሚና ተጫውታለች የሚለው እና ከባለቤትነት ጥያቄ ተያይዞ የሚነሱ ክሶች የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት እንዲሻክር ከማድረግ ባለፈ መሰረተ ቢስ ናቸው ብሏል፡፡
በመግለጫው መሰል ክሶች በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ባሉ ጥቂትና እሱን ለማሳካት ያልተፈለገ እርመጃ ከመውሰድ በማይታቀቡ ቡዱኖች የሚቀነቀኑ ናቸውም ብሏል፡፡
ሱዳን በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት የምታስበው ለአካባቢያዊ ሰላምና መረጋጋት ካላት ቁርጠኝነት የመነጨ መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስረድቷል።
የኢጋድ የወቅቱ ሊቀ መንበር ጠቅላይ ሚኒሰትር ዓብደላ ሃምዶክ ዋና አላማ የኢትዮጵያን አንድነትና መረጋጋት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በትግራይ ግጭት የተሳተፉ ሁሉም ኃይሎች ተኩስ አቁመው ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት እንዲደረግ ነው ብሏል መግለጫው፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ለሚነሱ ማናቸውም ችግሮች ያለውን ኮሚዩኒኬሽን ወሳኝና መሰረት ሆኖ ይቆያልም ብሏል፡፡
ሱዳን በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት መፍትሄ እስኪበጅለት የምታደረግውን ጥረት እንደምትቀጥልበትም ነው መግለጫው ያመላከተው፡፡
በትግራይ የተከሰተው ግጭት እንዲያበቃ የአከባቢውም ሆነ የዓለም ፍላጎት እንደመሆኑ ኢትዮጵያ የሱዳንን ጥረት በበጎ መልኩ እንድትመለከትው ስትልም ሱዳን ጠይቃለች፡፡
በዚህ ረገድ አማራጮችን ለመወሰን በሚልም ሱዳን በኢትዮጵያ የሚገኘው አምባሳደሯን ለምክር መጥራቷን መግለጫው አስታውቋል፡፡
ሱዳን የኢትዮጵያ መንግሥትን እና ህወሓትን ለማሸማገል ከማሰቧ በፊት ጦሯን ከኢትዮጵያ ማስወጣት እና መታመን እንዳለባት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በሰጠው መግለጫ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን ከሶሞኑ በሰጡት መግለጫ ሱዳን በዚህ ወቅት ለማደራደር ወሳኝ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የሆነውን ታዓማኒነት አታሟላም ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የፕሬስ ሴክሬታሪዋ የሱዳን ባለስልጣናት የካርቱም እና የአዲስ አበባ ግንኙነት እንዲሻክር ባደረጉበት በዚህ ወቅት ሱዳን ታማኝ አደራዳሪ ልትሆን እንደማትችልም ገልጸው ነበር።
ለማደራደር በቅድሚያ እነዚህ ነገሮች መፈታት እና መስተካከል እንዳለባቸውም ጭምር ቢለኔ ስዩም ተናግሯል።