ሃምዶክ መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ በቡርሃን ተሾመው የነበሩ የክልል ባለስልጣናትን በአዲስ ተኩ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ለውጦች ቢደርጉም እስካሁን “የቴክኖክራቶች ካቢኔ” አለመሰየማቸው ጥያቄ አስነስቷል
ሃምዶክ በጦር ኃይሉ የተሾሙትን አብዛኞቹን ሚኒስትር ዴዔታዎችንም በአዲስ ተክተዋል
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ቀደም ሲል በሌ/ጄ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን የተሰየሙ የክልል አስተዳዳሪዎችን በአዲስ ተኩ፡፡
ሃምዶክ ከክልል አስተዳደሮች በተጨማሪ እንደ ፈረንጆቹ በ2019 በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ተወግደው የነበሩትንና በጦር ኃይሉ የተሾሙትን አብዛኞቹን ሚኒስትር ዴዔታዎች እንዲሁም በአል በሽር አገዛዝ የነበሩ የቀድሞ ታጋዮችን መተካታቸውም ሲ.ጂ.ቲ.ኤን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጽ/ቤትን መረጃን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ውሳኔው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ከወታደሮቹ ጋር በተደረገ ስምምነት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መመለሳቸውን ተከትሎ በወታደራዊ ኃይሉ የተደረጉ ለውጦችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እያደረጓቸው ካሉ ጥረቶች አንዱ ነው ተብሎለታል፡
ሃምዶክ የተለያዩ ለውጦች በማድረግ ላይ ቢሆኑም፤ ከሳምንታት በፊት ከወታደራዊ ሃይሎች ጋር በተደረሰ ስምምነት መሰረት እስካሁን የቴክኖክራቶች ካቢኔን አልሰየሙም፡፡
ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ተቃዋሚዎች የተደረሰውን ስምምነት በመቃወማቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡
የሃምዶክ ወደ ስልጣን መመለስ የሱዳንን ፖለቲካዊ ቀውስ አልገታውም- ተመድ
በወርሃ ህዳር በካርቱም በተካሄደው የፖለቲካ ስምምነት ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ በተለያዩ 14 ጉዳዮች ላይ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከልም ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እና አንድ ወጥ የሆነ የሱዳን ጦር እንዲመሰረት፣ የሱዳንን ግዛታዊ አንድነት እንዲጠበቅ፣ የሽግግር ጊዜውን የሚመራውን ሕገ መንግሥታዊ፣ ህጋዊ እና ፖለቲካዊ አስራሮች መወሰን የሚሉት ይገኙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከስምምነቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ አንድነት ለሱዳን አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት፤ የሱዳን ጥቅም ማስጠበቅ ቀዳሚ ጉዳይ እንደሆነም አሳስበዋል።
“የተፈረመው ስምምነት ለሳምንታት የተሰራ የጠንካራ ስራ ውጤት ነው” ያሉት ሀምዶክ፤ “ሱዳን ምንም መመለስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ብትደርስም መመለስ እንደምትችል ያረጋገጠ ነው”ም ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አል ቡርሀን በበኩላቸው “የተፈረመው ስምምነት የሱዳናውያን የስራ ውጤት ነው፤ ይህ የእውነተኛ ሽግግር ጅማሮ ነው” ማለታቸው አይዘነጋም።
ብዙዎች “መፈንቅለ መንግስት ነው” ባሉት እርምጃ የሱዳን ጦር ባሳለፍነው ወር የሀገሪቱን የሽግግር መንግስት የሚመሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ጨምሮ ሲቪል ባለስልጣናትንና ከፍተኛ አመራሮችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል።