ከኒውዮርክ ስብሰባ በኋላ የግብጽ እና ሱዳን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ቤልጅየም እና ሩሲያ አቀኑ
ሚኒስትሮቹ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ዋነኛ የመወያያ አጀንዳቸው ያደርጋሉ ተብሏል
ሱዳን ሩሲያ በቀይ ባህር ወደብ የጦር ሰፈር እንድትገነባ ልትፈቅድ ትችላለች ተብሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የጸጥታው ምክርቤት በኢትጵያ ግድቡ ዙሪያ በኒውዮርክ ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ የግብጽ እና ሱዳን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ቤልጅየም እና ሩሲያ አቅንተዋል፡፡
የጸጥታው ምክርቤት ኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን አለመግባባት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሆነው እንፈቱት አሳስቦ ነበር፡፡ ምክርቤቱ በጉዳይ ላይ ጣልቃ ሊገባ የቻለው፣ ግብጽና ሱዳን የግድቡ ጉዳይ የአለምአቀፍ የደህንነት ስጋት ነው የሚል ሃሳብ በማቅረባቸው ነው፡፡
የግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ ወደ ቤልጅየም ሲያቀኑ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሬም አልሳዴቅ ደግሞ ወደ ሩሲያ ማቅናታቸው ተገልጿል።
የግብጽፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አህመድ ሀፊዝ እንዳሉት በሳሜህ ሽኩሪ የተመራ ልኡክ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ትብብሮችን ለማድረግ ወደ ብራሰልስ አቅንቷል። ሚኒስትሩ የግብጽ ፕሬዘዳንት አልሲሲ ለአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት የጻፉትን መልዕክትም እንደሚያደርሱ ተገልጿል።
ሽኩሪ በብራስልስ ቆይታቸው ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ሌሎች ከህብረቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩም ተገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሬም አልሳዴቅ ወደ ሩሲያ ማቅናታቸው ተገልጽል። እንደ ሩሲያው ስፑትኒክ ዘገባ ከሆነ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ትናንት ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ሩሲያ አቅንተዋል።
ሚኒስትሯ በሞስኮ ቆይታቸው ከሩሲያ አቻቸው ሰርጊ ላቭሮቭ ጋር በህዳሴው ግድብ፤ሩሲያ በሱዳን ልትገነባ ስላሰበችው ወታደራዊ ቤዝ እና ሌሎች ሁለትዮሽ እና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
ሱዳን በፕሬዘዳንት ኦማር አልበሽር የስልጣን ዘመን ሩሲያ በሱዳኗ ቀይ ባህር ወደብ ላይ የጦር ቤዝ አንድትገነባ ስምምነት ፈጽመው የነበረ ሲሆን በሱዳን አዲስ መንግስት መመስረቱን ተከትሎ ስምምነቱ ችግር ገጥሞት ነበር።
በዚህ ምክንያትም የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ስምምነቱን ያለመቀበል ፍላጎት ማሳየቱን ተከትሎ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቦ ነበር።
ወደ ሩሲያ ያቀኑት የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሞስኮ ቆይታቸው በዚህ ወታደራዊ ስምምነት ትግበራ ዙሪያ እንደሚወያዩ ዘገባው ጠቁሟል።ሚኒስትሯ ከዚህ በተጨማሪም በሞስኮ ቆይታቸው ሩሲያ በህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያን አቋም እንድታስቀይርላት ትጠይቃለችም ተብሏል።
የሁለቱ ሀገራት የብራሰልስ እና ሞስኮ ጉብኝት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ጣልቃ ይግባ በሚል ላቀረቡት ጥያቄ፣ ም/ቤቱ ልዩነቶች በአፍሪካ ህብረት ስር ይፈቱ የሚለውን የኢትዮጵያን አቋም ከደገፈ በኃላ ነው፡፡