ኢትዮጵያ በአማካኝ በአንድ ሰከንድ 900 ሜትር ኪዩብ ውኃ ወደ ተፋሰሱ ሀገራት እንደሚለቀቅ ገልጻለች
ሱዳን በዚህ ዓመት ሃምሌ ወር ከጥቁር ዓባይ አምስት ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ማግኘቷን የሀገሪቱ የጎርፍ ኮሚቴ አስታወቀ።
ኮሚቴው ካርቱም ከጥቁር ዓባይ ባለፈው ዓመት 7 ነጥብ 8 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ማግኘቷን ገልጻ ቁጥሩ በዚህ ዓመት ልዩነት እንዳለው አስታውቋል።
ባለፈው ዓመት ሀምሌ ወደ ሱዳን በገባውና በዚህ ዓመት ወደ ሀገሪቱ በደረሰው የውኃ መጠን መካከል የ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ልዩነት መኖሩንም ነው የሀገሪቱ ጎርፍ ኮሚቴ ይፋ ያደረገው።
ይሁንና በኢትዮጵያ ተከዜ የሚባለው እና ሱዳን ሲገባ አትባራ ከሚባለው ወንዝ ወደ ካርቱም የገባው ውኃ አራት ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፤ ከባለፈው ዓመት ሀምሌ ወር ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ብልጫ እንዳለውም ነው የተገለጸው።
ሱዳን የጥቁር ዓባይን ውኃ በምትለካበት አዴም በሚባለው ጣቢያ ዛሬ ወደ ሱዳን የገባው ውኃ 600 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፤ ከተከዜ ወይም ከአትባራ ደግሞ 230 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር ወደ ሱዳን መግባቱን ማረጋገጧን ይፋ አድርጋለች።
ሱዳን የጥቁር ዓባይ ወደ ሀገሯ የገባው የውኃ መጠን ከባለፈው ዓመት መቀነሱን ብትገልጽም፤ ኢትዮጵያ ግን ለታችናው ተፋሰስ ሀገራት (ግብጽ እና ሱዳን) በሕዳሴ ግድብ ሁለት የውሃ ማስተንፈሻዎች በዓመት 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚያገኙ ማስታወቋ ይታወሳል።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፤ የግድቡን 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅን በማስመለክት እንዳስታወቁት በሕህዳሴ ግድብ ሁለት የውሃ ማስተንፈሻዎች በአማካኝ በአንድ ሰከንድ 900 ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚለቀቅ መናገራቸው ይታወሳል።
ይህም የግድቡ ሁለቱ የውሃ ማስተንፈሻዎች በቀን ውስጥ 100 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ገደማ የሚደርስ ውሃ እንደሚለቁ ነው ሚኒስትሩ በወቅቱ የገለጹት።
ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት እና ለሌሎች ግልጋሎቶች ቢውልም፤ በተለይ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንደ ውኃ ባንክ እንደሚያገለግል ገልጸው ነበር።
ይህም የዓባይ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በየዓመቱ የማይቆራረጥ እና የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸውም የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የግድቡ የውሃ ሙሌት በክረምት ወቅት የሚከናወን እንደመሆኑ ሀገራቱን ከጎርፍ አደጋ እየተከላከለ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዘንድሮው የውሃ ሙሌት ከፍተኛ የዝናብ መጠን በመኖሩ ግድቡ ቶሎ መሙላቱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ ይህ ደግሞ በተለይም ሱዳንን ከጎርፍ አደጋ ተከላክሏል ብለዋል።
አሁን ላይ ግን ግድቡ ሞልቶ በመፍሰሱ ሱዳናውያን የውሃ እጥረት ያጋጥመናል ከሚል አላስፈላጊ ስጋት ወጥተው ራሳቸውን ከጎርፍ አደጋ ሊጠብቁ እንደሚገባ የገለጹት ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፤ ውሃ ከመያዝ በዘለለ ለኢትዮጵያ ትልቁ ስኬት ሀይል ማመንጨት በመሆኑ ለዚህ የሚሆን በቂ ውሃ መያዙንም ማረጋገጣቸው ይታወሳል።
በሱዳን ግድቦች ምን ያህል የውኃ መጠን አለ?
ሱዳን በግድቦቿ የያዙትን የውኃ መጠን ይፋ ያደረገች ሲሆን ከሕዳሴ ግድብ ቀጥሎ በሱዳን ብሉናይል ግዛት ባለው የሮሰሪስ ግድብ 560 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ መኖሩን አረጋግጣለች።
በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ሲናር ግዛት የሚገኘው ሲናር ግድብ 500 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር፤ ካርቱም የሚገኘው የጀበል አውሊያ ግድብ 85 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር፤ በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ከሰላ ግዛት የሚገኘው የገርባ ግድብ ደግሞ 230 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ መያዛቸው ተገልጿል።
ካርቱምን አልፎ የሚገኘው መረዌ ግድብ 525 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መያዙን ካርቱም ገልጻለች፡፡
አሁን ላይ በካርቱም ያለው የጥቁር ዓባይ የውኃ ከፍታ 15 ነጥብ 72 ሜትር ሲሆን ይህ መጠን 16 ነጥብ 50 ሜትር ከሆነ ጎርፍ እንደሚከሰት ተገልጿል።
የጎርፍ ኮሚቴው ሁሉም ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።