አሜሪካ እና ሱዳን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተወያዩ
ሳማንታ ፓወር በተመሳሳይ አጀንዳ ላይ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒሰትር አብደላ ሃምዶክ ጋር ትላንት መምከራቸው ይታወሳል
ሁሉም ኃይሎች ተኩስ አቁመው የኢትዮጵያን አንድነት ባስጠበቀ ወደ ውይይት መግትን እንደሚደግፉም ሀገራቱ ገልጸዋል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒሰትር አብደላ ሃምዶክ በኢትዮጵያ ጉዳይ መምከራቸው ተገለጸ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጋር የስልክ ቆይታ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ብሊንከን በቆይታቸው አሁን “በኢትዮጵያ አስከ አማራ እና ዓፋር ክልሎች ስለተስፋፋው ግጭት፣ አሳሳቢ ስለሆነው የትግራይ ሰብዓዊ እርዳታ ሁኔታ፣ ወደ ትግራይ እየተመለሱ መሆናቸው እየተነገረላቸው ስላለ የኤርትራ ኃይሎች ” በተመለከተ ከሃምዶክ ጋር እንደከሩም ነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ የገለጹት።
ቃል አቀባዩ በትግራይ ግጭት ተወናይ የሆኑ ኃይሎች ተኩስ አቁመው የኢትዮጵያን አንድነት ባስጠበቀ መልኩ ወደ ድረድር እንዲመጡና ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲያካሂዱ እንዲሁም እገዛ ሚያስፈልጋቸው ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች ለዚህም አሜሪካና ሱዳን ድጋ እንደሚያደርጉ ብሊንከንና ሃምዶክ ከስምምነት መድረሳቸውን አስታውቀዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒሰትር አብደላ ሃምዶክ በቆታቸው በሱዳን ዴሚክራሲያዊ የሽግግር ሂደት እና የአሜሪካ-ሱዳን ሁለትዮሽ ግንኙነት እንደተወያዩም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
በትናንትናው ዕለት በካርቱም ቆይታ ያደረጉት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር በተመሳሳይ አጀንዳ ላይ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዓብደላ ሃምዶክ ጋር መምከራቸው ይታወሳል።
አስተዳዳሪዋ ሳማንታ ፓወር ድጋፎችን ለሚፈልገው የትግራይ ህዝብ ማድረስ ካስፈለገ ሁሉም አካላት ግጭቶቹን ሊያቆሙ ይገባል ብለዋል።
ሳማንታ ፓወር የህወሓት ኃይሎቹን በአስቸኳይ ከአማራ እና አፋር ክልሎች ለቀው እንዲወጡ እንዲሁም የአማራ ክልል መንግስት ኃይሎቹን ከምዕራባዊ ትግራይ እንዲወጡ አሜሪካ ጥሪ ታቀርባለችም ነው ያሉት።
የኤርትራ መንግስት ኃይሎቹን ከኢትዮጵያ በአስቸኳይ እና በዘላቂነት እንዲያስወጣም ጭምር መጠየቃቸውም ተሰምቷል።