ሃምዶክ ለ2 ቀናት የያዙትን የኢትዮጵያ ጉብኝት በግማሽ ቀን አጠናቀው ወደ ሱዳን ተመለሱ
ከጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ጋር በነበራቸው ውይይት በኢጋድ በኩል አስቸኳይ ስብሰባ ለመጥራት እና የግድቡን ድርድር ለመቀጠል ተስማምተዋል
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉብኝት መርሃ ግብር ለምን በግማሽ ቀን እንደተጠናቀቀ የተገለጸ ነገር የለም
ዛሬ ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተው የነበሩት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መሃመድ አብደላ ሃምዶክ እና ልዑካቸው ጉብኝታቸውን በግማሽ ቀን አጠናቀው ወደ ሃገራቸው ተመለሱ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ2 ቀናት በሚል የያዙትን የጉብኝት መርሃ ግብር ለምን በግማሽ ቀን አጠናቀው እንደተመለሱ የተገለጸ ነገር የለም፡፡
ጉብኝቱን በተመለከተ መግለጫ የሰጠው የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በመግለጫው ስለዚህ ጉዳይ አላነሳም፡፡
አጭር ያሉትን ጉብኝት አጠናቀው መመለሳቸውን በሰጡት የቪዲዮ መግለጫ ያስታወቁት የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዑመር ገመረዲን ጉብኝታችን በሁሉም መመዘኛ የተሳካ ነበር ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ተገናኝተው ተወያይተን ነበር ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሃምዶክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር የተናጠል ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ ሌሎቹ ልዑካን ተቀላቅለው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የጋራ ውይይት አድርገናልም ነው ያሉት ገመረዲን፡፡
በተቻለ መጠን በቀጣናዊው የበይነ መንግስታት ተቋም ኢጋድ በኩል በአስቸኳይ ስብሰባ እንድናደርግ እና ቀደም ሲል የተቋቋመውን የኢትዮ-ሱዳን ከፍተኛ የጋራ የድንበር ኮሚቴን በቶሎ ወደ ስራ ለማስገባት ተስማምተናልም ብለዋል፡፡
ኮሚቴው በሚቀጥለው ሳምንት በካርቱም ስብሰባ እንደሚያርግም ነው የገለጹት፡፡
በአንዳንድ የአካሄድ ልዩነቶች ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት እንዲቀጥል ተስማምተናል ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አጭር ያሉት የዛሬው ጉብኝት ፍሬያማ እንደነበር ገልጸዋል ወደፊት በውይይቱ በተነሱት እና በሌሎችም ጉዳዮች ውጤታማነት ላይ ተስፋ ማድረጋቸውን በመጠቆም፡፡
በሃምዶክ ጉብኝት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የብሔራዊ ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተሩ ሌተናል ጄኔራል ጀማል አብዱል መጅድ፣ ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ካሊድ አብዲን አልሻሚ እና የወታደራዊ መረጃ ዳይሬክተሩ ሜጀር ጄኔራል ያሲር ሙሃመድ ኦስማን ተካተው እንደነበር አል ዐይን አማርኛ ዛሬ ጠዋት መዘገቡ ይታወሳል።