የሱዳን መንግስት እና አማጺያን የመጨረሻ የሰላም ስምምነት በቀጣዩ መስከረም 22 ይፈራረማሉ
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሃምዶክ ከቀናት በፊት ከአንድ አማጺ ቡድን ጋር በአዲስ አበባ ተስማምተዋል
በሱዳን መንግስት እና በአማጺያን መካከል ላለፉት 17 ዓመታት በተደረገ ውጊያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ሞተዋል
የሱዳን መንግስት እና አማጺያን የመጨረሻ የሰላም ስምምነት በቀጣዩ መስከረም 22 ይፈራረማሉ
በሱዳን መንግስት እና አማጺያን መካከል የመጨረሻ የሰላም ስምምነት መስከረም 22 በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ እንደሚፈረም የሰላም ድርድሩ ኃላፊ ገለጹ፡፡
የድርድር ቡድኑ ኃላፊ እና የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት የፀጥታ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ቱት ጋትሉዋክ “ጥቅምት 2 (በአውሮፓውያኑ) በመንግስት እና በሰላም ድርድሩ ሂደት ውስጥ ባሉ ወገኖች መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት የመጨረሻ ፊርማ የሚደረግበት ቀን ነው” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
የሱዳን ባለሥልጣናት እና የአማጺ ቡድኖች ጥምረት የሆነው የሱዳን አብዮታዊ ግንባር (ኤስ.አር.ኤፍ./SRF) ፣ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን በተለይም በምዕራብ ዳርፉር የተከሰተውን ግጭት ለማስቆም የታቀደ ታሪካዊ የሰላም ስምምነት በአውሮፓውያኑ ባለፈው ነሐሴ 31 ጁባ ውስጥ ተፈራርመዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ 2011 የተቋቋመው ኤስ.አር.ኤፍ. በጦርነት ከተጎዳው የምእራብ ዳርፉር ክልል እና እንዲሁም ከደቡብ የሀገሪቱ ክፍል የብሉ ናይል እና የደቡብ ኮርዶፋን ግዛቶች አማጺያንን ያሰባሰበ ነው፡፡
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሃምዶክ በጁባ በተደረገው ድርድር ለመስማማት ፈቃደኛ ካልሆነው የሱዳን ሕዝባዊ ነፃነት ንቅናቄ-ሰሜን (ኤስ.ፒ.ኤል.ኤም./SPLM-N) አማጺ ቡድን ጋር በኢትዮጵያ ውስጥ የተለየ ስምምነት መፈራረማቸውን የሁለቱ ወገኖች ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡
የሱዳን የረጅም ጊዜ መሪ ኦማር አልበሽር ፣ ለወራት የዘለቀውን ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ፣ እ.አ.ኤ. ሚያዚያ 2019 ከስልጣን ሲወገዱ ወደ ኃላፊነት የመጣው የሱዳን የሽግግር መንግስት ከዓማጺያን ቡድኖች ጋር የሰላም ስምምነት ላይ መድረስን ቀዳሚ ተግባሩ አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ስምምነቱ በዋነኝነት በፀጥታ ፣ በመሬት ባለቤትነት ፣ በሽግግር ፍትህ ፣ በስልጣን ማጋራት እና በጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የተሰደዱ ሰዎችን መልሶ ማቋቋም ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በተጨማሪም የአማጺ ኃይሎችን ማፍረስ እና ተዋጊዎቻቸውን ወደ ብሔራዊ ጦር ስለማቀላቀልም ይመለከታል፡፡
እ.ኤ.አ. በ 2003 አማጺያን መሳሪያ ካነሱ በኋላ በዳርፉር ብቻ በተካሄደው ውጊያ 300,000 ያህል ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ከጥቅምት 2019 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ ደቡብ ሱዳን በሱዳን መንግስት እና በዳርፉር ፣ ደቡብ ኮርዶፋን እና ብሉ ናይል ግዛቶች በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች መካከል ሽምግልና ስታደርግ ቆይታለች፡፡