ኤሚሬትስ በረመዳን ወር በኢትዮጵያ ከ2,000 በላይ ለሚሆን ቤተሰብ የምግብ ድጋፍ አደረገች
የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ከዩኤኢ ጋር በቅርበት ለመስራት አቅዷል
ሀገሪቱ በትናንትናው እለት ለ300 ቤተሰቦች የሚሆን የምግብ ሸቀጦች ድጋፍ አድርጋለች
ኤሚሬትስ በረመዳን ወር በኢትዮጵያ ከ 2,000 በላይ ለሚሆን ቤተሰብ የምግብ ድጋፍ አደረገች
በኤምሬትስ የሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ለሚገኙ ችግረኛ ቤተሰቦች ፣ ወላጅ አልባ ልጆች እና ስደተኞች ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬትስ ኤምባሲ አማካኝነት በረመዳን ወር ለ2,000 ዜጎች የምግብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ አምባሳደር መሐመድ ሳሊም አህመድ አል ራሺዲ እንዳሉት ይህ የሰብዓዊ ዕርዳታ በካሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ፋውንዴሽን ፣ በዛይድ የበጎ አድራጎት እና ሰብአዊ ሥራዎች ፣ በሻሪቃ የበጎ አድራጎት ማህበር እና የበጎ አድራጎት ተቋም የቀረበ ነው፡፡
ኤምባሲው ትናንት ለ ሴቶች ፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ያስረከበው የምግብ ነክ ሸቀጦች ድጋፍ በአማራ ክልል ለ 300 ቤተሰቦች እንደሚከፋፈል ሚኒስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የተደረጉ ድጋፎችም በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ ቤተሰቦች መከፋፈላቸውን ነው ወ/ሮ ፊልሰን የገለጹት፡፡
ዩኤኢ ለኢትዮጵያ የምታደርገው የበጎ አድራጎት ተግባር የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ ይህም የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት እና ወዳጅነት የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጎልበት እና ለማስቀጠል የሴቶች ፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላም ፣ ከዩኤኢ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት እቅድ መያዙን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
ባለፈው አርብ እለት የሻሪቃ የበጎ አድራጎት ማህበር ከዩኤኢ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ለሚገኙ 100 ኤርትራውያን ስደተኞች የምግብ ዕርዳታ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ኢንቨስት በማድረግ ላይ የምትገኘው ዩኤኢ ለኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በተለያዩ ጊዜያት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል እና ህክምና የሚውሉ በርካታ ቁሳቁሶችን በቅርቡ ድጋፍ ማድረጓም ይታወቃል፡፡