“የጊዜ ጉዳይ ነው እንጅ ጥሩ ምርጫ ማድረጋችን አይቀርም” የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን
በዘንድሮው ምርጫ 50 ሚሊዮን ህዝብ ይሳተፋል ብሎ ቦርዱ አቅዶ ነበር
ብልጽግናና ህወሓት ቦርዱ ምርጫውን ሲያራዝም የቫይረሱ ሁኔታ ሳይታይ ለምን ወደ ዉሳኔ አንሄዳለን ብለው ነበር
ብልጽግናና ህወሓት ቦርዱ ምርጫውን ሲያራዝም የቫይረሱ ሁኔታ ሳይታይ ለምን ወደ ዉሳኔ አንሄዳለን ብለው ነበር-የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን
ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ጠቅላላ ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት እንደማይካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ምርጫው መደረግ በነበረት ጊዜ አለመደረጉ፤ምርጫ በየአምስት አመቱ እንደሚካሄድና የመንግስት ስልጣንም በአምስት አመት ውስጥ ያበቃል ብሎ በደነገገው ህገመንግስት ጉዳይ ጥያቄም ተነስቷል፡፡ከ106 የሕገ መንግስት አንቀጾች በሦስቱ ላይ ትርጉም እንዲሰጥባቸው መወሰኑን ተከትሎ የባለሙያዎችና የባለድርሻ አካላት አስተያየት ሲደመጥ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አንዱ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱ ማንኛውንም አይነት የምርጫ አይነቶችና የህዝበ ውሳኔዎች የማደራጀት ኃላፊነትን ለመወጣት የመራጮች ምዝገባን በ30 ቀናት ውስጥ ፣የዕጩዎች ምዝገባን በ14 ቀናት ውስጥ የምረጡኝ ዘመቻን በ90 ቀናት ውስጥ፣ለመራጮች የሚሰጥ ትምህርትን በ120 ቀናት ያህል ለማከናወን ታስቦ እንደነበር ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አቅርበዋል፡፡
በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ 50 ሚሊዮን መራጮች እንደሚሳተፉ ቅድመ ግምት እንደነበር የገለጹት ምክትል ሰብሳቢው 50 ሺ ምርጫ ጣቢያና 250 ሺ ምርጫ አስፈጻሚ መልምሎና አሰልጥኖ ለማሰማራት ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም በኮሮና ምክንያት ግን ዝግጅቶቹ ባለማለቃቸው የወረቀት ላይ ሥራዎችን በተግባር ማከናወን እንዳልተቻለ አስታውቀዋል፡፡
ወረርሽኙ ስጋት ተወግዶ እንዲሁም ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደገና ግምገማ በማድረግ አዲስ የምርጫ ስራ ዕቅድና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቃሴውን እንደሚያስጀምር ለተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቁንም አንስተዋል፡፡በወረርሽኙ ስጋት የማይስተጓጎሉ ስራዎችን እንደሚሰራም ቦርዱ ማሳወቁን አንስተዋል፡፡
በአጠቃላይ ለምርጫው የሚያስፈልገው የሰው ሃይል ብዛት 180 ሺ የነበረ ቢሆንም ወደ 240 ሺ ከፍ እንዲል የተደረገ ሲሆን ሲሆን አጠቃላይ ሂደቱ 3 ወራት ሊወስድ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
የሰው ኃይል ቁጥር እንደሚጨምር በተሰራው ዕቅድ መሰረት ከ2 ቢሊዮን 512 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚጠይቅ በማብራሪያው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት መደረጉንና ግብዓቶችን መስጠታቸውን አንስተዋል፡፡
ምርጫ ማድረግ እንደማይቻል ተገለጸ በኋላ በነበረው ውይይትም ፓርቲዎች ይህንን ጉዳይ ማንም የሚቆጣጠረው እንዳልሆነ እና ከአቅም በላይ እንደሆነ መረዳታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሁንና በዚህ ሰበብ መንግስት አላግባብ ስልጣኑን እንዳይጠቀም ማድረግ አለባችሁ የሚል አስተያየት መሰጠቱን አንስተዋል፡፡
ይሁንና የሀገሪቱ ገዥ ፓርቲ ብልጽግና እና የትግራይ ክልል ገዥ ፖርቲ ህወሓት ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ “ገና መጀመሪያው ላይ ነው ያለነው፣ይህ ነገር (የቫይረሱ ሁኔታ) ወደት እንደሚሄድ እንኳን ሳናይ ወደ ምርጫው ለውሳኔ ለምን እንሄዳለን የሚል ነገር አንስተው ነበር”ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ምርጫው በተለይ በኮሮና ምክንያት ብዙ የሰው ሃይልና ገንዘብ የሚጠይቅ እንደሆነ ያነሱት ሰብሳቢዋ “የጊዜ ጉዳይ ነው እንጅ ጥሩ ምርጫ ማድረጋችን አይቀርም“ብለዋል፡፡ህዝቡ ከእኛ የሚጠብቀውን ምርጫ በምንችልበት ጊዜ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡