11ኛ ሳምንቱን የደፈነው የሱዳን ጦርነት በካርቱም እና ዳርፉር ግጭቱ መበርታቱ ተገልጿል
ካርቱምና ኤል ጂኒና በተቀሰቀሰው ጦርነት የከፋ ጉዳት ደርሶባቸዋል
በሱዳን በተከታታይ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ሊቀጥሉ ባለመቻላቸው ውጊያው ተባብሷል
11ኛ ሳምንቱን የደፈነው የሱዳን ጦርነት በካርቱም እና ዳርፉር ግጭቱ መበርታቱ ተገልጿል።
በሱዳን ርዕሰ መዲና ግጭት፣ መድፍ እና የአየር ድብደባ መበርታቱን እማኞች ተናግረዋል።
ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝብን ያፈናቀለና ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለው በተቀናቃኝ ወታደራዊ አንጃዎች መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት 11ኛ ሳምንቱን ይዟል።
በምዕራብ ዳርፉር ክልል ትልቅ ከተማ በሆነችው በኒያላ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ከፍተኛ ግጭት መጨመሩን የአይን እማኞች ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በምዕራብ ዳርፉር በኤል ጂኒና ከማሳሊት ማህበረሰብ የመጡ ጎሳዎች ኢላማ እና ግድያዎች ላይ ቅዳሜ እለት ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።
ባለፈው ሳምንት በዳርፉር እና በኮርዶፋን አካባቢዎች ውጥረቱ እና ግጭቶች ተባብሰው የነበረ ቢሆንም፤ ዋና ከተማው ካርቱም እና ኤል ጂኒና በሚያዝያ 15 በሱዳን ጦር እና በፈጣኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት የከፋ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በጅዳ ባደራደሩት ውይይት የተደረሱ ተከታታይ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ሊቀጥሉ ባለመቻላቸው ውጊያው ተባብሷል። ንግግሮቹ ባለፈው ሳምንት ተቋርጠዋል።
ትልቅ በሆኑት በሦስቱ ከተሞች ካርቱም፣ ባህሪ እና ኦምዱርማን ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ እስከ እሁድ ጠዋት ድረስ ከባድ ጦርነት መቀጠሉን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በአብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራው ጦር በአየር ድብደባ እና በከባድ መሳሪያ በመሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ የሚመራውን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በመዲናዋ ከሚገኙ ሰፈሮች ለማባረር ሲሞክር ቆይቷል።