ቱርክ የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎችን ለማደራደር ያቀረበችው ሀሳብ ተቀባይነት አገኘ
የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን እና የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቅዳሜ ዕለት በፖርት ሱዳን ተወያይተዋል
ለ20 ወራት የዘለቀወን ጦርነት ለማስቆም በአሜሪካ እና ሳኡዲ የተመራው ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል
ሱን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መካከል ለሁለት አመታት ገደማ የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም ቱርክ ያቀረበችው የአደራዳሪነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሱዳን ሉዐላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሀን በቱርክ አደራዳሪነት ለውይይት ለመቀመጥ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሀን ከአል ቡርሃን ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር አንካራ በጦርነት በምትታመሰው አፍሪካዊት ሀገር ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የማገዝ ፍላጎት እንዳላት ተናግረው ነበር፡፡
ቅዳሜ እለት በፖርት ሱዳን ቡርሃን እና የቱርክ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቡርሃኔትቲን ዱራንን ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ጄነራል ቡርሀን የሱዳን አመራሮች የቱርክን አደራዳሪነት እንደሚቀበሉ ለቱርኩ ፕሬዝዳንት መልዕክታቸውን እንዲያደርሱላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን መጠየቃቸውን የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ የሱፍ ከስብሰባው በኋላ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
የቱርክ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዱራን በበኩላቸው የሰላም ሂደቱ የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልፀው፤ ሀገራቸው ይህንን ግጭት ለማስቆም ሌሎች የቀጠናው አካላትን በማሰባሰብ የበኩሏን ሚና ለመጫወት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል ።
በሱዳን ጦር ተቀባይነት ባገኘው የቱርክ የአደራዳሪነት ሚና ዙሪያ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሎ እስካሁን ተቃውሞውንም ሆነ ድጋፉን አልገለጸም፡፡
ከዚህ ቀደም አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ የመሩት የአፍሪካ ህብረት ፣አረብ ኤሜሬትስ እና ሌሎችም ሀገራት በታዛቢነት የተሳተፉበት ሁለቱን ተዋጊዎች ለማስማማት የተደረገው ጥረት ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
የሱዳን ጦር አዛዥ ከቀድሞ ምክትላቸው እና ከፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መሪ ጄነራል መሀመድ ሃምዳን ዳግሎ ጋር ለ20 ወራት ያደረጉት ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲገድል 12 ሚሊዮን ዜጎችን ደግሞ ከቀያቸው አፈናቅሏል፡፡
ሁለቱም ተዋጊ ሀይሎች በከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በሚከሰሱበት ጦርነት ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለከፍተኛ ርሀብ መጋለጣቸውን የተመድ ኤጄንሲዎች ሪፖርት ያመላክታል፡፡