በሱዳን የዳቦ ዋጋ መናሩን ተከትሎ ህዝባዊ ቁጣ ተቀሰቀሰ
የዳቦ አመጹ ተቃውሞዎችን ስታስተናግድ የነበረቸውን ሱዳን ወደ ተባባሰ ቀውስ እንይከታት ተሰግቷል
በሱዳን የዳቦ ዋጋ በ40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ የዳቦ አመጽ በመካሄድ ላይ ነው
በሱዳን የዳቦ ዋጋ መናሩን ተከትሎ ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጣ ተቀሰቀሰ፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የዓለም ነዳጅ እና ምግብ ዋጋዎችን እንዲንር አድርጓል፡፡
በሱዳንም የዳቦ ዋጋ ከጦርነቱ በፊት ከነበረበት አሁን ላይ 50 የሱዳን ፓውንድ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ይህም የአገሪቱን ዜጎች ለከፍተኛ ቁጣ ዳርጓል፡፡
በዚህም ምክንያት በሱዳን የዳቦ አመጽ በመካሄድ ላይ ሲሆን በሺህ የሚቆጠሩ ሱዳናዊያን ወደ አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ ናቸው፡፡
ባሳለፍነው ጥቅምት በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ (ዶ/ር) ይመራ በነበረው መንግስት ላይ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ስልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግስት ላይ ተጨማሪ ጫናን ይፈጥራል ተብሏል፡፡
መፈንቅለ መንግስቱን ለመቃወም ወደ አደባባይ የወጡት ሱዳናዊያን አሁን ደግሞ የዳቦ ዋጋ መናሩ ተጨማሪ ሱዳናዊያን ወደ አደባባይ ለተቃውሞ ወጥተዋል፡፡
የሱዳን የጸጥታ ሀይሎችም በአገሪቱ በርካታ ከተሞች ወደ አደባባይ የወጡ አመጸኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙን አልዓይን ከካርቱም ዘግቧል፡፡
ከዳቦ ዋጋ በተጨማሪም የነዳጅ ዋጋ በ50 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም በጀነራል አልቡርሃን ለሚመራው ወታደራዊ መንግስት ሌላኛው ፈተና ነውም ተብሏል፡፡
ተቃዋሚዎቹ ከዚህ በፊት ስልጣን በሀይል የተቆጣጠረው የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድር እንዲመልስ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
የዳቦ ዋጋ መናሩን ተከትሎ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ አንማርም ያሉ ተማሪዎችን ጨምሮ የባቡር መንገድ ሰራተኞችም የዳቦ አመጹን ተቀላቅለዋል፡፡
የሱዳን ጦር ስልጣን በሀይል መቆጣጠሩን ተከትሎ አሜሪካ ለሱዳን ልትሰጠው የነበረውን 700 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ማቆሟ ይታወሳል፡፡
በፈረንጆቹ 2019 በሱዳን የዳቦ ዋጋ ጨምሯል በሚል ተቃውሞ ተጀምሮ በስልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዘዳንት ኦማል ሀሰን አልበሽርን ከስልጣን እንዲነሱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑ አይዘነጋም፡፡