ተመድ በፖለቲካዊ ፍጥጫ ውስጥ ያሉት የሶማሊያ መሪዎች ውጥረቱን እንዲያረግቡ አሳሰበ
ተመድ ከፕሬዝዳንት ፋርማጆ እና ጠቅላይ ሚኒሰትር ሮብሌ ጋር በተናጠል እመከረ ነው ተብሏል
የሶማሊያ መሪዎች የፖለቲካ ፍጥጫ ሀገሪቱን ወዳልተፈለገ ቀውስ እንዳይከታት ተሰግቷል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) እና ሌሎች ሀገራት በፖለቲካዊ ፍጥጫ ውስጥ ያሉትን የሶማሊያ መሪዎች ያለውን ውጥረት እንዲቀንሱ አሳሰቡ፡፡
ተመድ እና አጋሮቹ ወደ ወታደራዊ ግጭት ሊያመራ ይችላል ያሉትን የሶማሊያ መሪዎች መሳሳብ ለማርገብ፤ ከሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዝዳንት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡
የሶማሊያ መንግስት ባለስልጣን እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሁሴን ሮብሌ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትሯ ሞሊ ፒ ጋር የሶማሊያ ፖለቲካን በማስመለከት በተናጠል መክሯል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒሰትሩ በተጨማሪ ከፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ /ፋርማጆ/ ጋር መነጋገራቸው በዚህም ሮብሌ የፓርላማ ምርጫ በፍጥነት እንዲያጠናቅቁ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸው የሞሊ ፒ ቢሮ በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው መልእክት አጋርቷል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የሶማሊያ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ አሪ ጋይታኒስ “የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አለም አቀፍ አጋሮች ውጥረቱን ለማርገብ ከሁሉም ወገኖች ጋር እየተገናኙ ነው” ብሏል።
ከሶማሊያ መሪዎች ጋር የሚደረግ ምክክር አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎችን ጨምሮ በሶማሊያ የሚገኙ የአለምአቀፍ አካል አጋሮችን ያሳተፈ መሆኑንም ጋይታኒስ ተናግሯል።
እሮብ እለት ቡድኑ ከፕሬዚዳንቱ እና ከፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጋር ለመወዳደር ካሰቡ የእጩዎች ቡድን ጋር በተናጠል ተገናኝቷልም ነው የተባለው።
ጋይታኒስ "የሁለቱም ስብሰባዎች ዋና ዓላማ የሶማሊያ መሪዎች የሀገሪቱን ጥቅም እንዲያስቀድሙ እና የምርጫ ጉድለቶችን በማረም ላይ እንዲያተኩሩ ማበረታታት ነበር"ም ብሏል፡፡
የሶማሊያ ፌደራል መንግስት ቃል አቀባይ መሀመድ ኢብራሂም ሙአሊሙ፡ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ስለ ሶማሊያ የፖለቲካ ሁኔታ፣ የጸጥታ እና ምርጫ ጉዳይ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፒ ጋር ጋር መምከራቸው በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አጋርቷል።
ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ሰኞ እለት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሙስና ጠርጥሬያቸዋለው በሚል ከስራ አግደው ነበር፡፡
በተቃራኒው እርምጃው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የማካሄድ ያክል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ ፤ሁሉም የጸጥታ ሃይሎች ከቢሯቸው ትዕዛዝ እንዲወስዱ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።
እሮብ እለት ለሁለተኛ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ግንኙነት ያላቸው የጸጥታ ሃይሎች በፕሬዚዳንት ቤተ መንግስት አቅራቢያ በሚገኝ አካባቢን ጨምሮ በከተማዋ እየታዩ እንደሆነም የሮይተርስ ዘግቦ ነበር፡፡