የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ ትናንት በራሳቸው ፈቃድ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል
የሱዳን መሪዎች ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው መግባባትን መፍጠር እንዳለባቸው በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።
ዋሸንግተን በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኩል ከሱዳን ሽግግር ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ስልጣን መልቀቅ በኋላ የመጀመሪያ አስተያየት ሰጥታለች።
በዚህም አሜሪካ፤ የሱዳን መሪዎች ልዩነትን ወደ ጎን በመተው መግባባትን ማስቀደም እና ለሲቪል አስተዳደር ቀጣይነት መረጋገጥ መስራት እንዳለባቸው ገልጻለች።
ቀጣዩ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር እና የካቢኔ አባላት ምርጫ በሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ መሰረት መከናወን እንዳለበትም ነው በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ያስታወቀው።
የጠቅላይ ሚኒስትር እና የካቢኔ አባላት ምርጫ ሕገ መንግስታዊ ድጋጌውን የተከተለ በማድረግ የዜጎችን የነጻነት፣ የሰላምና የፍትህ ግቦችን ማሳካት እንዳለበትም አሜሪካ ጠይቃለች።
ዋሸንግተን፤ ለዴሞክራሲ መወለድ እየጠየቀ ካለው የሱዳን ሕዝብ ጎን እንደምትቆም የገለጸች ሲሆን፤ በሰልፈኞች ላይ የሚደርግ ጥቃት እንዲቆምም አሜሪካ የሱዳን መንግስትን ጠይቃለች።
የሱዳን ሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ከስልጣን መልቀቃቸው የተገለጸ ሰሆን፤ በዚህ ውሳኔም የሀገሪቴ ዜጎች ግራ መጋባታቸው እየተገለጸ ነው።
አብደላ ሃምዶክ ከኃላፊነት ለመልቀቅ መልቀቂያ ማስገባት በሱዳን የፖለቲካ መሪዎች መካከል የነበረው ፍጥጫ የከፋ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ሁነኛ ማሳያ ስለመሆኑም እየተነገረ ነው።