ውይይቱ ሃገሪቱ ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ የምትወጣበትን መደላደል ለመፍጠር የሚያስችል ነው ተብሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በሱዳን የፖለቲካ ውይይቶችን ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ሊያመቻች ነው፡፡
ተመድ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች የሚያሳትፍ ውይይት ለማድረግ ያለውን እቅድ በተመለከተ አሳውቋል፡፡
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም ትናንት ቅዳሜ ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር ውይይቱን በተመለከተ አውርተዋል፡፡
ውይይቱን በተመለከተ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን የጉቴሬዝ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ቮከር ፐርዝስ አስታውቀዋል፡፡
ዓለም አቀፍ አጋሮችን የሚያሳትፈው የሱዳናውያኑ ምክክር ሃገሪቱን ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ለማውጣት የሚያስችሉ መንገዶችን ለማመቻቸት እንደሚያስችል ሂደቱን አስመልክተው ባወጡት መግለጫ አስቀምጠዋል፡፡
ፐርዝስ ተመድ የሱዳንን ሽግግር ለመደገፍ ያቋቋመው ተልዕኮ መሪም ናቸው፡፡
ከአል በሽር መወገድ በኋላ በሽግግር ሂደት ላይ ያለችው ሱዳን ከባድ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እንደገባች ይነገራል፡፡
በተለይ በአል ቡርሃን የሚመራው የሃገሪቱ ጦር በአብደላ ሃምዶክ ይመራ በነበረው የሽግግር መንግስት ላይ እርምጃዎችን ወስዶ ስልጣን መጨበጡ ቀውሱን የበለጠ እንዳባባሰውም ነው የሚነገረው፡፡
ሃምዶክ ወደ ስልጣናቸው ቢመለሱን የጦሩን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ይህን የጦሩን አካሄድ በመቃወም ካርቱምን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው፡፡ በሰልፎቹ 60 ገደማ ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ለተለያዩ ጉዳቶች ተዳርገዋል፡፡
ይህ ሁኔታ ሃገሪቱን የበለጠ ወደ መቀመቅ እንዳይከታት መስጋታቸውንፐርዝስ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን የተወሰዱ እርምጃዎች ሁኔታዎችን ሱዳናውያን ወደሚፈልጉት የሽግግር ሂደት ለመመለስ አለመቻላቸውንም ነው ፐርዝስ የተናገሩት፡፡
“ብጥብጡን አቁሞ ወደ አዲስ ምዕራፍ የመሸጋገሪያ ጊዜው አሁን ነው” ም ብለዋል፤ ውይይቱ አካታች እንደሚሆን በጠቆሙበት መግለጫቸው፡፡