የሱዳኑን ጦርነት ለማስቆም በጄኔቫ ሲደረግ የነበረው ድርድር ያለስምምነት ተጠናቀቀ
ድርድሩ ያለ ስምምነት ቢጠናቀቅም ተፋላሚዎቹ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ፈቅደዋል
በሱዳን እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት የተነሳ ከአስርተ አመታት ወዲህ በምድር አስከፊ ርሀብ ሊከሰት እንደሚችል ተነግሮ ነበር
በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የ16 ወራቱን የሱዳን ጦርነት ለማስቆም ሲደረግ የነበረው ድርድር ትላንት ያለ ስምምነት ተጠናቋል፡፡
በአሜሪካ እና ሳኡዲአረብያ አደራዳሪነት በተካሄደው ድርድር የፈጥኖ ደራሹ ልኡካኑን ቢልክም የሱዳን ጦር ግን ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ባለመሟላተቸው ሳይሳተፍ ቀርቷል፡፡
በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልክተኛ ቶም ፔሬሎ የመጀመርያው ዙር ድርድር ትላንት መጠናቀቁን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ድርድሩ ጦርነቱን በማስቆም ዙርያ ባይሳካም የሰብአዊ እርዳታ መተላለፍያዎች ይከፈቱ ዘንድ ውጤት እንዳስገኘ ተናግረዋል።
ሁለቱም ወገኖች አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታዎች ተደራሽ እንዲሆኑ እና ለንጹሀን ጥበቃ በማድረግ የሚኖራቸውን አፈጻጸም በቀጣይ እንገመግማለን ያሉት መልክተኛው፥ ለአሁኑ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሱዳናውያንን ህይወት ለመታደግ እድል አግኝተናል ብለዋል።
50 ሚሊየን ከሚጠጋው የሱዳን ህዝብ ግማሽ ያህሉ በረሃብ ውስጥ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ኤጄንሲዎች ባወጧቸው ሪፖርቶች ማመላከታቸው ይታወሳል፡፡
ኤጄንሲዎቹ በሀገሪቱ በፍጥነት ሰብአዊ ድጋፎች መሰራጨት ካልጀመሩ በፈረንጆቹ 1985 በኢትዮጵያ ከተከሰተው አስከፊው ረሀብ የሚበልጥ የሚሊየን ሰዎችን ህይወት ሊቀጥፍ የሚችል ረሀብ ሊከሰት እንደሚችል ሲያስጠነቅቁ ሰንብተዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት አሜሪካ ፣ ሳኡዲ አረብያ ፣ የአፍሪካ ህበረት፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና ግብጽ የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማስፈጸም እያደረጓቸው ከነበሩ ውይይቶች ጎን ለጎን የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ በሚደርስበት ሁኔታ ላይም ጠንካራ ምክክር ሲያደርጉ መቆየታቸውን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
በዚህም በምዕራብ ድንበር አቋርጦ ወደ ዳርፉር የሚሄድ ፣ በሰሜን በኩል ከፖርት ስዳን ወደ ዳባር የሚጓዝ በደቡብ ሲናር የሚያቋርጥ ሶስት የእርዳታ ኮሪደሮችን ለማስከፈት ስምምነት ላይ መደረሱ ተሰምቷል፡፡
በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልክተኛ ቶም ፔሬሎ እነዚህ ሶስት መተላለፍያዎች ለ20 ሚሊየን ሱዳናውያን ምግብ ፣ መድሀኒት እና የነፍስ አድን ቁሳቁሶችን ለማድረስ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡
እርዳታ የሚያደርሱ ተሸከርካሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ እና ነጻ የስርጭት ሂደት እንዲኖር ሁለቱም ተፋላሚዎች ተስማምተዋል ያሉት ልዩ መልክተኛው አፈጻጸሙን አሜሪካ እና ሌሎች የድርድሩ ተሳታፊዎች በቅርበት እንደሚከታተሉ ነው የገለጹት፡፡
የአለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ እንደሚያመላክተው በአሁኑ ወቅት 25.6 ሚሊየን ሱዳናውያን በአጣዳፊ ርሀብ ውስጥ ሲገኙ ከ755ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለከፍተኛ ርሀብ ተጋልጠዋል፡፡
የጄኔቫው ድርድድር በሁለተኛ ዙር የሚካሄድ ሲሆን ድርድሩ የሚካሄድበት ትክክለኛ ቀን አልታወቀም፡፡ በተጨማሪም በዚህኛው ዙር ሁለቱ ወገኖች ፊት ለፊት ይገኛኙ እንደሆነ የተባለ ነገር የለም፡፡
በአሜሪካ የሚመራው እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር የሚሳተፍበት ይህ ስብሰባ በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2023 የተጀመረውን እና 50 ሚሊዮን ከሚሆነው የሱዳን ህዝብ ግማሽ ያህሉ ለምግብ እጥረት እንዲዳረግ ምክንያት የሆነው ጦርነት እንዲቆም የማድረግ አላማ አለው።