በጦርነት እየታመሰች ያለችው ሱዳን የግብርና ሚኒስትር በሀገሪቱ ረሀብ የለም አሉ
ረሀብ የሚታወጀው ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ሲያጋጥመው፣ ህጻናት ሲጎዱ እና ሞት ሲመዘገብ ነው
ሚኒስትሩ 750ሺ የሚሆኑ ሱዳናውያን በከፍተኛ የምግብ እጥረት ውስጥ ላይ ናቸው የሚለውን የተመድ መረጃ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል
በጦርነት እየታመሰች ያለችው ሱዳን የግብርና ሚኒስቴር በሀገሪቱ ረሀብ የለም አሉ።
በሱዳን ረሀብ የለም ያለት የግብርና ሚኒስትሩ 750ሺ የሚሆኑ ሱዳናውያን በከፍተኛ ረሀብ ውስጥ ላይ ናቸው የሚለውን የተመድ መረጃ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል።
በሱዳን መሪ በሚመራው የሱዳን ጦር እና ሰፊ የሚባል የሀገሪቱን ክፍል በተቆጣጠረው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር መካከል ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሱዳን ከዓለም ከባድ የሚባለውን የምግብ እጥረት ቀውስ እያስተናገደች ነው።
"755ሺ ከአጠቃላይ ህዝብ አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም...ያንን ረሀብ ብለው መጥራት አይችሉም" ብለዋል የግብር ሚኒስትሩ አቡ በከር አል ቡሽራ በፖርት ሱዳን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ።የሱዳን ህዝብ ብዛት 50 ሚሊዮን ነው።
የሱዳን ጦር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በተቆጣጠረው ቀጣና እርዳታ እንዳይገባ እና ንግድ እንዳይካሄድ እግድ ጥሏል። የተመድ፣ የቀጣናዊ አካላት እና እርዳታ ድርጅቶች በጥምረት የፈጠሩት ኢንተግሬትድ ፉድ ሴኩሪቲ ፌዝ ክላሲፊኬሽን(አይፒሲ) ባለፈው ሀምሌ ወር መጨረሻ ግማሽ ያህሉ የሀገሪቱ ህዝብ በከፍተኛ የምግብ እጥረት ውስጥ መሆኑን እና በሀገሪቱ ያሉ 14 ቦታዎች የረሀብ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ገልጾ ነበር።
ረሀብ የሚታወጀው ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ሲያጋጥመው፣ ህጻናት ሲጎዱ እና ሞት ሲመዘገብ ነው።
አል ቡሽራ የተመድ ባለሙያዎች በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በተያዙ ቦታዎች ያላቸውን መረጃ የመተንተን ብቃት ጥያቄ ውስጥ አስገብተዋል፤ የምግብ እጥረት መኖሩን የሚያሳዩ ጠቋሚዎች ገና አልተወሰኑም ብለዋል።
የአይፒሲን መረጃ ተከትሎ ገለልተኛ ኮሚቴ በሱዳን ረሀብ ተከስቷል ብሎ ሊያውጅ እና የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የሱዳንን ጦር ገደብ ጥሶ እርዳታ እንዲያደርስ ሊያነሳሳው ይችላል ተብሏል።
አልቡሽራ ግን መንግስት እንዲህ አይነት ሁኔታዎችን እንደማይቀበል ገልጸዋል።
አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ በሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች መካከል ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። አሜሪካ በቅርቡ ሁለቱን ኃይሎች በስዊዘርላንድ እንዲገኙ እና እንዲነጋገሩ ጥሪ አቅርባለች። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በንግግሩ ለመገኘት ፍቃደኝነቱን አሳይቷል።