የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ አዛዦች በየፊናቸው በጎረቤት ሀገራት ጉብኝት እያደረጉ ነው
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) አዛዡ ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ጂቡቲ ገብተዋል።
ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ከጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ መምከራቸውን በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ጦርነት እንዲቆም እንደሚፈልግና የሱዳን ህዝብን ሰቆቃ ለመጨረሻ ጊዜ የሚቋጭ ሁሉንአቀፍ መፍትሄ ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ መሆኑን ለፕሬዝዳንት ኦማር ጊሌ እንደነገሯቸውም ጠቁመዋል።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የጀመረው ጥረት ውጤታማ ሆኖ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንም ለድርድር ዝግጁ ነን ብለዋል።
ኦማር ሀሰን አልበሽርን በጋራ ከመንበራቸው ያነሱት ጀነራል አብዱልፈታል አልቡርሃን እና ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ጦር ከተማዘዙ ዘጠኝ ወራት ተቆጥረዋል።
የጦርነቱ መነሻ ሄሜቲ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) የሱዳን ጦርን ይቀላቀል ወይንም ትጥቁን ይፍታ የሚል ውሳኔ መተላለፉ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ሺዎችን ለህልፈት ዳርጎ፤ ካርቱምን አፈራርሶ፤ ሚሊየኖችን ተፈናቃይ ያደረገው ጦርነት በጂዳ በተደረሱ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነቶች በረድ ከማለቱ ውጭ አልቆመም።
በቅርብ ሳምንታትም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል ዋድ መዳኒን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞችን መያዙን መግለጹ ይታወሳል።
ጦርነቱ በቀጠለበት ወቅት የሱዳን ጦር አዛዡ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ መሪ ሄሜቲ በጎረቤት ሀገራት ጉብኝት ማድረጋቸው ውጥረቱ እየረገበ ሊሄድ እንደሚችል ተገምቷል።
ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ በቅርቡ በኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ጀነራል አልቡርሃንም በህዳር ወር በኢትዮጵያ እና ግብጽ ጉብኝት ማድረጋቸው አይዘነጋም።
ሁለቱም ተፋላሚዎች በየፊናቸው እያደረጓቸው የሚገኙ ጉብኝቶች ኢጋድ እና ጎረቤት ሀገራት የጀመሩትን ተፋላሚዎቹን የማቀራረብ ጥረት እንደሚያግዝ ይታመናል።
ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ዛሬ የጎበኙዋት ጂቡቲም ሁለቱን ተፋላሚ ሃይሎች ፊት ለፊት ለማገናኘት ለቀጣዩ ጥር ወር ቀጠሮ ይዛለች።