ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍ ለመቀንስ ወሰነች
አሜሪካ በ2019 ለኢትዮጵ 824 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሰጠች አስታውቃለች
የአሜሪካ ዉሳኔ ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ሊያሻክር እንደሚችል ተገምቷል
ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍ ለመቀንስ ወሰነች
70ኛው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትት ማይክ ፖምፔዮ ሀገራቸው ለኢትዮጵያ ከምትሰጠው ድጋፍ የተወሰነው እንዲቆም ማጽደቃቸውን ፎሬይን ፖሊሲ ዘገቧል፡፡ ይህም በዋናነት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባቸው ካለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው በዘገባው የተካተተው፡፡
በዚህም መሰረት አሜሪካ ለኢትዮጵያ የተለያዩ ዘርፎች ከምትሰጠው ድጋፍ 130 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ወደ አዲስ አበባ እንዳይላክ ሊደረግ ይችላል፡፡ ይህ የአሜሪካ ውሳኔ በአዲስ አበባና በዋሸንግተን መካከል የነበረውን የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳያሻክረው ተሰግቷል፡፡
ሀገሪቱ ልታቆም ያሰበችው ለጸጥታ ፣ ለጸረ ሽብር ዘመቻ፣ ለወታደራዊ ትምህርትና ልምምድ ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል እና ለልማት የምትሰጠውን ድጋፍ እንደሆነ የአሜሪካ ባለሥልጣናትና የኮንግረንስ ሰዎች መናገራቸውን ፎሬይን ፖሊሲ ገልጿል፡፡ ይሁንና ለድንገተኛ ሰብዓዊ ድጋፍ፣ ለምግብ ድጋፍ፣ ለጤና በተለይም ለኮሮና እና ኤች.አይ.ቪ መከላከል የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ይቀጥላል ነው የተባለው፡፡
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከግብጽ ጎን በመቆም ኢትዮጵያን ለመጉዳት አልሟል ማለታቸውን ፎሬይን ፖሊሲ ጽፏል፡፡ ትራምፕ ለሲሲ ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ፣ በቡድን 7 ሀገራት ስብሰባ ላይ አብዱል ፋታህ አልሲሲን “ተወዳጅ አምባገነን“ ማለታቸውን ዘገባው በማሳያነት ገልጿል፡፡
በግድቡ ጉዳይ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በሚል የትራምፕ አስተዳደር ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የበጀት ድጋፍ ለመቀነስ ወስኖ በግብጽ ላይ ግን መሰል እርምጃ አለመውሰዱም ለዚህ ማሳያ ተደርጓል፡፡
የዋሸንግተን ሰዎች ሀገራቸው በድርድሩ ላይ ገለልተኛ መሆኗን ቢገልጹም ይህ ግን በኢትጵያም በግብጽም በኩል ተቀባይነት አላገኘም፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት በዚህ ጉዳይ ላይ ለኮንግረንሱ በሰጡት ማብራሪያ “የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ጠንካራ ሆኖ ይቀጥላል ፤ ምክንያቱም ዋሸንግተን ከወዳጅ ሀገራት ጋር ጠንካራ ውይይት ታደርጋለች” ብለዋል፡፡ በአንድ በኩል ድጋፍ እያቋረጡ በሌላ በኩል ወዳጅነት አይቀንስም ማለት “ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው” ሲሉ አንድ የኮንግረስ አባል ገልጸዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2019 አሜሪካ 824 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጓ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 497 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ለሰብዓዊ ድጋፍ መዋሉን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ገልጿል፡፡
አሁን ላይ አሜሪካ አቋርጣለሁ ባለቸው ድጋፍ ምክንያት ኢትዮጵያ በግድቡ ድርድር ላይ ያላትን አቋም ልትቀይር ትችላለች ብሎ ማሰብ እንደማይቻል አንዳንድ የአሜሪካ ባስልጣናት ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ግድቡ ለኢትዮጵያ ያለው ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ ጠቀሜታ ነው፡፡