ካርቱም፤ የወቅቱ ሊቀመንበር “አልቡርሃን ናቸው” ብላለች
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የጠሩትን ስብሰባ ሱዳን ተቃውማለች።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፤ ኢጋድ በጠራው ስብሰባ ላይ ሀገሪቱ እንደማትሳተፍ እና እንደማይመለከታት አስታውቋል።
ካርቱም ስብሰባውን የተቃወመችው ስብሰባው መጠራት ያለበት በወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር በሱዳን እንጅ በዋና ፀሀፊው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እንዳልሆነ ገልጻለች።
የኢጋድ ሊቀመንበር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የፕሬዝዳንቶች ጉባዔ ጠርተው የነበረ ቢሆንም፤ ይህንን ስብሰባ ሱዳን እንደማትሳተፍ ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አሊ ሳዲቅ ተናግረዋል።
የኢጋድን ስብሰባ ከወቅቱ ሊቀመንበር ከሱዳን ውጭ ማንም መጥራት እደማይችልም ነው ያስታወቀው። ከዚህ በተጨማሪም በተጠራው ጉባዔ ላይ ሱዳን አጀንዳ መሆን እንደሌለባትም ነው የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
የወቅቲ የኢጋድ ሊቀመንበር ሱዳን ስትሆን ይህንንም ሲመሩ የነበሩት የቀድሞው የሀገሪቱ ሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ነበሩ።
አሁን ላይ ሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ባይኖራትም የወቅቱ ሊቀመንበር፤ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አብደል ፈታህ አልቡርሃን እንደሆነ አስታውቃለች።
የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ በሱዳን ከኢጋድ ልዑክ መሪ ጋር ተገናኝተዋል ተብሏል።