በሱዳን መንግስት ከተመረጠ በኋላ ጦሩ ወይም ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች በፖለቲካ ውስጥ ይሳተፋሉ ብለው እንደማያስቡ ገልጸዋል
ከአውሮፓውያኑ 2023 በኋላ የሱዳን ጦር ከሀገሪቱ ፖለቲካ እንደሚወጣ ሉኣላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበሩና የጦር ኃይሎች አዛዡ ሌፍተናንት ጄነራል አብደል ፈታህ አልቡርሃን አስታወቁ።
በሱዳን ምርጫ እንደሚደረግ ቀደም ብሎ የተገለጸ ሲሆን ምርጫው ከተካሄደ በኋላ የሀገሪቱ ጦር በፖለቲካው እንደማይሳተፍ ተገልጿል።
አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በቀጣይ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ከስልጣን የተወገደው የቀድሞው አስተዳደር ምንም አይነት ሚና እንደማይኖረው ገልጸዋል።
በመፈንቅለ መንግስት ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱን አፍርሰውት የነበሩት አልቡርሃን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ከወሰኑ በኋላ በቀጣይ ዓመት በፖለቲካ እንደማይሳተፉ ተናግረዋል።
በሱዳን መንግስት ከተመረጠ በኋላ ጦሩ ወይም ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች በፖለቲካ ውስጥ ይሳተፋሉ ብለው እንደማያስቡ ገልጸዋል።
የጦሩ በፖለቲካ አለመሳተፍ ተፈጥሯ ሁኔታ የሚደግፈው እና በስምምነቱ ላይ የተቀመጠ እንደሆነም የሽግግር ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።
በአብደል ፈታህ አልቡርሃን የተመራው የሱዳን መፈንቅለ መንግስት የሽግግር መንግስቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ከስልጣን አንስቶ የነበረ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ጫና መበራከት ምክንያት ሃምዶክ ወደ ቢሯው መመለሳቸው ይታወሳል።
የሽግግር መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሲቪል አስተዳደሩ ወደቦታው እንዲመለስ ከአልቡርሃን ጋር ስምምነት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ይህም በርካታ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል።
ይህንን ስምምነት በተመለከተ ከሲኤንኤን ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት ሀምዶክ ምንም እንከን የሌለበት ስምምነት ከመጠበቅ እንከኖች ያሉበት ስምምነት ማድረግ እንደሚሻል ገልጸዋል።
አብደል ፈታህ አልቡርሃን በወቅቱ አብደላ ሃምዶክን ከስልጣን አንስተው የነበረ ቢሆንም ምዕራባውያን ግን የምናውቀው የሽግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክን ብቻ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ከእነዚህ ጫናዎች በኋላም ሃምዶክ ከቤት ውስጥ እስር ወደ ንግስታዊ ወንበራቸው ተመልሰዋል።