ሌ/ጀነራል አልቡርሃን በሱዳን ብሄራዊ ደህንነት ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ስምንት ጀነራሎችን ከስራ አግደዋል
የሱዳን ጦር ዋና አዛዥ የደህንነት አመራሮችን ከስራ ማገዳቸው ተሰምቷል።
የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ሉዓላዊ ፕሬዝዳንት ሌትናል ጀነራል አል-ቡርሃን ስምንት የሱዳን ብሄራዊ ደህንነት ጀነራሎችን ከስልጣን ማንሳታቸውም ነው የተነገረው።
ከስልጣን የተነሱት የደህንነት ጀነራሎች በቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር የስልጣን ጊዜ ጀምሮ በስራ ላይ እንደነበሩ ተገልጿል።
ጀነራል አልቡርሃንም ከስልጣን ባገዷቸው የደህንነት ጀነራሎች ምትክም በጦሩ ውስጥ የነበሩ የደህንነት ባለሙያዎችን መተካታቸውን አስታውቀዋል።
ይሁንና ጀነራል አልቡርሃን ለምን ከዚህ ውሳኔ ላይ እንደደረሱ እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን ጦሩ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ከሱዳናዊያን እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት በኋላ ስልጣን ከሲቪል አስተዳድሩ ጋር መጋራቱን ተከትሎ የመጣ ሊሆን እንደሚችል እየተገለጸ ይገኛል።
የሱዳን ጦር ከአንድ ወር በፊት በፈጸመው መፈንቅለ መንግስት ስልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ ከተለያዩ አካላት በተደረገበት ግፊት ስልጣን መልሼ አጋራለሁ ቢልም አሁንም ሱዳናዊያን የአገሪቱ ጦር ከፖለቲካ ራሱን ያውጣ ሲሉ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
በጦሩ እና ሲቪል አስተዳድሩ መካከል በተደረገው ስምምነት መሰረት ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ቢስማሙም የሱዳን ጦር አሁንም ከእስር ያልለቀቃቸው ፖለቲከኞች እንዳሉ ተገልጿል።