“አብደላ ሀምዶክ እስር ቤት ሳይሆን እኔ ቤት ነው ያለው” ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አልቡርሀን
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎች በእስር እንደሚቆዩና ሌሎቹ ግን እንደሚፈቱ ገልፀዋል
በሱዳን የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነገሮች ሲረጋጉ ይነሳል ብለዋል
የሱዳን ጦር አዛዥ ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን ከሰዓታት በፊት መግለጫ ሰጥተዋል።
ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን በመግለጫቸውም በሱዳን ጦር በቁጥጥር ስር የዋሉት ጠቅላይ ሚኒስትር በአብደላ ሀምዶክ ያሉበትን አስታውቀዋል።
በዚህም “ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እኔ ቤት ነው ያለው” ያሉት ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን፤ “ይህ የሆነውም ለደህንነታቸው ሲባል ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክን ወደ ቤታቸው የወሰዱትም የደህንነት ስጋት ስለነበረ እንደሆነ ያስታወቁት አልቡርሃን፤ “በየቀኑ እተገናኝ እየነጋገርን ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
ለጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ክብር አለን ያሉት አል ቡርሃን፤ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ እንደሚሰሩም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ የፖለቲካ ገደብ ስለተጣለባቸው ስራቸውን በነጻነት መስራት እንደማይችሉም አስታውቀዋል።
የሱዳን ጦር አዛዥ ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን በመግለጫቸው አክለውም በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎች በእስር ቤት እንደሚቆዩ ገልጸው፤ ሌሎቹ ግን ከእስር እንደሚለቀቁ አስታውቀዋል።
በሱዳን በትናትናው እለት የአስቸኳይ ጊዝ አዋጅ መታወሱን አስታውሰው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ነገሮች ሲረጋጉ ይነሳል ሲሉም አስታውቀዋል።