“ሱዳንን ለማሸነፍ የሚችል ኃይል የለም”- አል ቡርሃን
የትናንቱን መፈንቅለ መንግስት “ያከሸፈውን ጦሩን፤ ከሽግግር ሂደቱ ገለል አድርጎ ሱዳንን በብቸኝነት ሊመራ የሚችል አካል” እንደማይኖርም ነው ያስጠነቀቁት
የሱዳን ጦር ጠቅላይ አዛዡ “ሱዳንን ማንም በብቸኝነት ሊመራ አይችልም” ብለዋል
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን “ሱዳንን ማንም በብቸኝነት ሊመራ አይችልም”ሲሉ ተናገሩ፡፡
አል ቡርሃን የሃገሪቱን ጦር ኃይል ማንም ገለል ሊያደርገው እንደማይችልም አሳስበዋል፡፡
ጠቅላይ አዛዡ “አመከንን” ያሉትን የትናንቱን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በማስመልከት ዛሬ በሰጡት መግለጫ ሙከራው የመከነው በጦሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ጦራችን ተገቢውን መሰረተ ልማት ትጥቅ አሟልቷል፤ ይህን አቅሙን ለማሳደግ እንዲጠቀምበትም እንፈልጋለን” ነው በመግለጫቸው ያሉት፡፡
ቡርሃን የጦሩ አንድነት መጠበቅና መጠናከር ለሱዳን አንድነት ዋስትና ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ማንም አካል ጦሩን ገለል ሊያደርገው እንደማይችል ነው ቡርሃን የገለጹት፤ ጦሩ የሃገሪቱ እና የአንድነቷ “ጠባቂ” መሆኑን በመጠቆም፡፡
የትናንቱን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ “ሌላ ማንም ሳይሆን ጦሩ ነው ያመከነው”ም ብለዋል፡፡
ቡርሃን የጋራ ወታደራዊ ልምምዶቹ ውስጣዊ አንድነታችንን አጠናክረውታል ያሉም ሲሆን “ሱዳንን ሊያሸንፍ የሚችል ኃይል የለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከሽግግር ሂደቱ ገለል አድርጎ ሱዳንን በብቸኝነት ሊመራ የሚችል አካል እንደማይኖርም ነው የገለጹት፡፡
የአል በሽር አገዛዝ ከተወገደበት ህዝባዊ አቢዮት በኋላ አፈንጋጭ አካሄዶችን የሚከተሉ የፖለቲካ ኃይሎች እንዳሉ በማስታወስም “ማንም አካል ጠቅልሎ እንዲገዛ ” እንደማይፈቅዱ አስጠንቅቀዋል፡፡
አል ቡርሃን ትናንት ከግልበጣ ሙከራው በኋላ በደቡባዊ ካርቱም አል ሻጃራ አካባቢ የሚገኘውን የጦር ካምፕ ጎብኝተው፤ ከጦሩ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
አል ሻጃራ ሙከራው ከተጀመረባቸው የጦሩ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
የጦሩን 21 መኮንኖች ጨምሮ በሙከራው የተሳተፉ በርካቶች እንደተያዙ ሱዳን ማስታወቋ የሚታወስ ነው፡፡
በቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ህዝባዊ እና ሲቪል መንግስት እንዲመሰረት አይፈልግም፤ ስልጣኑን አሳልፎ ለመስጠትም ዝግጁ አይደለም በሚል ይተቻል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ከሚመራው መንግስታዊ አካል ጋር ትልቅ ቅራኔ ውስጥ እንደሚገኝም ነው የሚነገረው፡፡
የግብጹን ፕሬዝዳንት የአብዱል ፈታህ አል ሲሲን ፈለግ በመከተል ወታደራዊ መንግስትን የማቋቋም ፍላጎት አለው በሚል የሚተቹትም በርካቶች ናቸው፡፡
ከሲቪሊያን እና ከጦሩ አመራሮች በተውጣጡ 11 አባላት ወርሃ ነሐሴ 2011 ዓ/ም ላይ የተዋቀረው የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት በ39 ወራት ውስጥ ማለትም እስከ ቀጣዩ ዓመት ህዳር ድረስ ምርጫ አካሂዶ አዲስ መንግስት እንዲመሰረት የማስቻል ሃራዊ ኃላፊነት አለበት፡፡