ሱዳን በሰልፈኞች ላይ የተፈጸመውን ጥሰት እየመረመረች መሆኑን ጠ/ሚ አብደላ ሃምዶክ ገለፁ
የፖለቲካ እስረኖች እንዲለቀቁ እና ሰላማዊ ሰልፎኞች እንዲከበሩም ጠ/ሚ ሃምዶክ ጥሪ አቅርበዋል
ሃምዶክ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ በጦር ኃይሉ የተሰጡ አዳዲስ ሹመቶችን ይገመግማሉ ተብሏል
በሱዳን የተደረገውን የፖለቲካ ስምምነት ተከትሎ ወደ ቀድሞ ኃላፊነታቸው የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒሰትር አብዳላ ሃምዶክ፤ ካለፈው ጥቅምት 25/2021 ወዲህ ሱዳን በሰልፈኞች ላይ የተፈጸመውን ጥሰት እየተመረመረ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የወጣው መግለጫ እንደሚመክተው ከሆነ ሃምዶክ ይህንን ያስታወቁት ወታደራዊ ኃይሉን ይቃወሙ ከነበሩትና ሲቪሉ ክንፍ ጥምረት አንድ አካል ከሆኑት የነፃነት እና የለውጥ ኃይሎች ጋር በትናንት ምሽት ከተወያዩ በኋላ ነው።
የሱዳን ጦር የሲቪል አስተዳደሩ ላይ መፈንቅለ ምንግስት በፈፀሙን ተከትሎ በሱዳን በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከ40 በላይ ሰዎች በሀገሪቱ ጦር መገደላቸው ይታወሳል።
የነፃነት እና የለውጥ ኃይሎች ቡድን የተደረሰው የፖለቲካ ስምምነት እውን ለማድረግ ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ አንዲኖር እና ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ ተደረጉ ሹመቶች ውድቅ እንዲደረጉ የሚል ግልጽ አቋሙን በውይይቱ ወቅት አንጸባርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተር አብደላህ ሀምዶክ እና የነፃነት እና የለውጥ ኃይሎች ቡድን በስምምነቱ መሰረት የፖለቲካ እስረኖች እንዲለቀቁ እና ሰላማዊ ሰልፎች እንዲከበሩ የሚል ጥሪም አቅርበዋል።
ከዚህም በተጫማሪ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ በጦር ኃይሉ የተሰጡ አዳዲስ ሹመቶችን እንደሚገመግሙ ተገልጿል።
የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በሀገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግስት ከተፈፀመ ሶስት ሳምንታት በኋላ ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የሚያስችል የፖለቲካ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
ሌተናል ጀነራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሀን እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላህ ሃምዶክ በ14 ጉዳዮችን ዙሪያ መፈራረማቸውም ነው የተገረው።
ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከልም ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እና አንድ ወጥ የሆነ የሱዳን ጦር መመስረት፣ የሱዳንን ግዛታዊ አንድነት ማስጠበቅ፣ የሽግግር ጊዜውን የሚመራውን ሕገ መንግሥታዊ፣ ህጋዊ እና ፖለቲካዊ አስራሮች መወሰን የሚሉት ይገኙበታል።
በሱዳን መሪዎች መካከል የተደረገው ሱዳን የፖለቲካ ስምምንት በተመድ፣አፍሪካ ህብረት፣ አውሮፓ ህብረት፣ ኢጋድ እና ሌሎች ሀገራት ዘንድ አድናቆት ተችሮታል።