ጠ/ሚ አብደላ ሀምዶክ አሁንም የሱዳን ሕጋዊ መሪ መሆናቸውን የአውሮፓ ህብረት ገለፀ
የአውሮፓ ህብረት በሱዳን ተካሄደ የተባለውን መፈንቅለ መንግስት አውግዟል
የአውሮፓ ህብረት ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አበደላ ሀምዶክ ጋር መገናኘት አፈልጋለሁ ብሏል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብደላ ሀምዶክ አሁንም የሱዳን ሕጋዊ መሪ መሆናቸውን የአውሮፓ ህብረት ገለጸ።
ባሳለፍነው ሰኞ በተደረገ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተነሱት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና የካቢኔ አባሎች የሽግግር መንግስቱ ሕጋዊ መሪዎች መሆናቸውን ዕውቅና እንደሚሰጥ የአውሮፓ ሕብረት አስታውቋል።
- አፍሪካ ህብረት፤ የሱዳን የሽግግር ምክር ቤት ወደነበረበት እስኪመለስ ድረስ ካርቱም ታግዳ እንደምትቆይ አስታወቀ
- በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተነሱት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከእስር ተለቀቁ
በካርቱም የሚገኘው የአውሮፓ ህብረት ልዑክ በሱዳን የተደረገውን መፈንቅለ መንግስት ከሚያወግዙ ወገኖች ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዳለው ገልጿል።
ህብረቱ ከፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ፣ ኖርዌይ፣ ስፔን፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድ፣ ብሪታኒያ እና አሜሪካ ኤምባሲዎች ጋር በመተባበር መግለጫ ሰጥቷል።
የሱዳን ሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትና በወታደሩ ከስልጣን የተነሱት ሃምዶክ ወደ መኖሪያ ቤታቸው መመለሳቸውን ብናውቅም፤ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም መዘግየት ከእስር እንዲፈቱ እንጠይቃለን ሲል ሕብረቱ አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ካቢኔያቸውን የሽግግር መንግሥቱ ሕገ መንግሥታዊ መሪዎች ስለመሆናቸው አሁንም ዕውቅና መስጠታችንን እንቀጥላለን ሲልም ነው የገለጸው።
መቀመጫቸውን በካርቱም ያደረጉ አምባሳደሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ ቢገናኙ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ያነሳው መግለጫው፤ ከአብደላ ሃምዶክ ጋር በአስቸኳይ እንዲንገናኝ እንጠይቃለን ብሏል።
በተጨማሪም ህብረቱ ሁሉም የሱዳን ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መሰረታዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ እንዲሁም የጸጥታ እና ሌሎች የታጠቁ ሃይሎች ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች ላይ ጥቃቶችን እንዳያደርሱ ጠይቋል።
በመላ ሀገሪቱ የሰብአዊ አቅርቦትን ያለገደብ እንዲሰራጭ የጠየቀው የህብረቱ መግለጫ፤ በተለይም በእነዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዓለም አቀፉ የሰብአዊ ማህበረሰብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሱዳናውያን የሚያደርገውን የማድረስ ስራ ቀጣይነት እንዲሆን በሱዳን ውስጥ ያለ የማንኛውም ባለስልጣን ዋና ተግባር መሆን እንዳለበትም ሕብረቱ አሳስቧል።
በህገ መንግስታዊ ሰነዱ እና በጁባ የሰላም ስምምነት ላይ እንደተገለፀው የሱዳን የዴሞክራሲ ሽግግር ፍኖተ ካርታ በአስቸኳይ እንዲመለስም ሕብረቱ ጠይቋል።
በሱዳን ሽግግር ውስጥ በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል ሁሉን አቀፍ፣ሰላማዊ እና ህገ-መንግስታዊ ውይይት መደረግ አለበትም ተብሏል።