ሱዳን ብሔራዊ ስምምነትን ለማምጣት በሚል ያሰረቻቸውን ፖለቲከኞች ልትለቅ ነው
እስረኞቹን በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚለቀቁ የሱዳን ጦር መሪ አል ቡርሃን አስታውቀዋል
ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት ሲባል የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚለቅ የሱዳን ጦር አስታወቀ፡፡
እርቅና መግባባትን ለማምጣት ሲባል እስረኞቹ በቀጣዮቹ ሁለትና ሶስት ቀናት ውስጥ እንደሚለቀቁ የጦሩ መሪና የሃገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን አስታውቀዋል፡፡
ቡርሃን የእስረኞቹን መለቀቅ በተመለከተ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ በመግለጫው እስረኞቹን ለመልቀቅ የሚያስችሉ ሂደቶች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
እስረኞቹን ከመልቀቅ ጋር በተያያዙ የህግና የፍትህ ጉዳዮች ላይ ከሃገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መምከራቸውንም ነው ቡርሃን የገለጹት፡፡
የሃገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ስምምነት ላይ የሚደርሱና የሚግባቡ ከሆነ ጦሩ ስልጣን ለመልቀቅና ለሲቪሊያን ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ጦሩ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ይመራ የነበረውን የሲቪሊያን የሽግግር መንግስት አስወግዶ ስልጣኑን ከተቆጣጠረበት ካሳለፍነው ጥቅምት መጨረሻ ጀምሮ ሱዳን በነውጥ ላይ ነች፡፡
ኢትዮጵያ፤ሱዳን ያለባትን ውዝፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ እንድትከፍል ጠየቀች
ጦሩ እርምጃውን ገትቶ ስልጣኑን ለሲቪሊያን እንዲያስረክብ ደጋግመው የጠየቁ ሱዳናውያንም ወደ አደባባዮች በመውጣት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማትም የተለያዩ ጫዎችን ሲያደርጉ ነበረ፡፡
ሆኖም ሃምዶክን ወደ ስልጣን መልሶ የነበረው ጦሩ ዳግም በማባረር የራሱን የሽግግር ምክር ቤት አባላትን መምረጡና መሾሙ ይታወሳል፡፡
ይህ ግን እምብዛም ከጫና አልታደገውም፡፡ ሁሉንም የሚያግባባ የሲቪል መንግስት ይመስረት የሚሉ ጫናዎችም በርትተዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ይመስላል ለእርቅና ብሔራዊ መግባባት ዝግጁ ነን የሚሉት የጦሩ አመራሮች ያሰሯቸውን ፖለቲከኞች ለመልቀቅ የወሰኑት፡፡