በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጭነው ወደ ካርቱም የገቡ “ጦር መሳሪያዎች ተያዙ” መባሉ “ከእውነት የራቀ” ነው - የሱዳን የሃገር ግዛት ሚኒስቴር
ተገቢው የጉምሩክ ክሊራንስ ሂደት መጀመሩንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው
ሚኒስቴሩ ባለስልጣናቱ ያዝን ያሉት “ጦር መሳሪያ” ምንም ዐይነት የህግ ግድፈት እንደሌለበት አስታውቋል አስታወቀ
የሱዳን ጉምሩክ ባለስልጣናት ያዝን ያሉት “ጦር መሳሪያ” ራሳቸው በሰጡት ህጋዊ ፈቃድ ተጓጉዞ ወደ ካርቱም የገባ እንደሆነ የጦር መሳሪያዎቹ ባለቤት የሆነውና ‘ዋዒል ሸምሰዲን’ የተባለው የንግድ ተቋም አስታወቀ፡፡
የተቋሙ ጠበቃ የሆኑት ሲራጁዲን ሃሚድ ተያዙ የተባሉትን ጦር መሳሪያዎች በህጋዊ መንገድ እንደገቡ መግለጻቸውን የአል ዐይን ኒውስ የካርቱም ዘጋቢ ያገኛቸው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
‘ዋዒል ሸምሰዲን’ ለሲቪል ግልጋሎት የሚውሉ ጦር መሳሪያዎችን ከውጭ የማስገባት እና የመነገድ ፈቃድ ያለው ድርጅት ነው፡፡
የሩሲያው ጦር መሳሪያዎች አምራች ‘ክላሽንኮቭ ኮንሰርን’ የሱዳን ወኪል ሆኖም ይሰራል እንደ ጠበቃው ሲራጁዲን ገለጻ፡፡
አል ዐይን እንዳገኘው የሲራጁዲን መግለጫ ከሆነ ሞስኮው የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቢሮ እና ዋዒል ሸምሰዲን እ.ኤ.አ በ2019 ነው፤ 290 የአደን ጥይቶችን የያዙ 73 ካርቱኖችን ሞስኮው ከሚገኘው ዶሞዴዶቭ አየር ማረፊያ ወደ ካርቱም ለማጓጓዝ የተስማሙት፡፡
ሆኖም ካርቱኖቹ በተባለው ቀን ተጓጉዘው ካርቱም ለመድረስ አልቻሉም፡፡
ይህን ተከትሎ ‘ዋዒል ሸምሰዲን’ ጉዳዩ በካርቱም ወደሚገኝ ፍርድ ቤት ወስዶ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከሷል፡፡
‘250 ሺ የአሜሪካ ዶላር ካሳ ይክፈለኝ’ ሲልም ነበር ተቋሙ የጠየቀው፡፡
በሱዳን ዜና አገልግሎት (ሱና) የቀረበው ዘገባ የተዛባ እና ከእውነት የራቀ ነው ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ምላሽ የሰጠው አየር መንገዱ በተገቢ የስምምነት ሰነዶች በአደራ የተረከብኳቸው ናቸው ያላቸው ካርቱኖቹ በኢትዮጵያ የደህንነት አካላት ተይዘው ለረዥም ጊዜ በአዲስ አበባ መቆየታቸውን አስታውቋል፡፡
በዚሁ መሰረት ካርቱኖቹ በተገቢው የህግ መንገድ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጭምር እንዲያውቀው ሆኖ ባገኘው ፈቃድ ወደ ካርቱም ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ምሽት ተጭነው መግባታቸውን ነው ያስታወቀው፡፡
ሆኖም የሱዳን የጉምሩክ ባለስልጣናት የምሽት ባይኖኩላር መነጽሮችን ጨምሮ 73ቱን ካርቱኖች በአል በሽር አገዛዝ ደጋፊዎች የገቡ ሳይሆኑ እንዳልቀረ ጠርጥሬያለሁ በማለት ይዟቸዋል፡፡
የሱዳን ባለስልጣናትና ሚዲያዎች አስቀድሞ ዕውቅናና ይሁንታ ያለውን ይህን ጉዳይ እንዲህ ማድረጋቸው ሆን ብለው የኢትዮጵያን እና ኩራቷ የሆነውን የአየር መንገዷን ስም ለማጠልሸት በማሰብ ነው ያለው በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ድርጊቱ የሱዳንን ህዝብ የማወናበድ እና በሁለቱ ሃገራት ህዝቦች መካከል የቆየውን የወንድማማች ግንኙነት የመጠልሸት አደጋ አለው ብሏል።
በዚህ ረገድ ኤምባሲው ፍላጎት ላለው አካል አስፈላጊ ሰነዶችን ለመስጠት ዝግጁነቱ መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡
ጉዳዩን የተመለከተ መግለጫ ዘግይቶ ያወጣው የሱዳን የሃገር ግዛት ሚኒስቴር የጉምሩክ ባለስልጣናቱ ያዝን ያሉት “ጦር መሳሪያ” ‘ዋዒል ሸምሰዲን’ ያለምንም የህግ ግድፈት ወደ ካርቱም ያስመጣው እንደሆነ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተገቢውን የህግ ሂደት ሳይጠብቁ ወደ ካርቱም ያስገባቸው ናቸው በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች ጭምር የሚናፈሰው መረጃ “ከእውነት የራቀ” እንደሆነም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡
ንብረቶቹን ላስመጣቸው እና ህጋዊ ፈቃድ ላለው ‘ዋዒል ሸምሰዲን’ ለማስረከብ ተገቢው የጉምሩክ ክሊራንስ ሂደት መጀመሩንም ገልጿል፡፡