ሱዳን ከዛሬ ጀምሮ ሽብርን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር በይፋ ወጣች
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሱዳን ከሽብር መዝገብ እንድትሰረዝ ከ 2 ወራት በፊት ፈርመው ነበር
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሱዳንን ሽብርን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር መሰረዙ ተገለጸ
አሜሪካ ሱዳንን በመንግስት ደረጃ ሽብርን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር እንድትወጣ የሚያስችል ፊርማ መፈረሟን አስታወቀች፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሱዳን እንድትሰረዝ ከወሰኑበት ጊዜ አንስቶ ጉዳዩን ለአሜሪካ ኮንግረስ የማሳወቂያው የ45 ቀናት ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፒዮ ሀገሪቱ ከዛሬ ጀምሮ በይፋ እንድትሰረዝ መፈረማቸው ተገልጿል፡፡ ይህም በፌዴራል መዝገብ እንደሚታተም በካርቱም የአሜሪካ ኤምባሲ ይፋ አድርጓል፡፡
ናይሮቢ እና ዳሬ ሰላም በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ለደረሰው የሽብር ጥቃት ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች እንድትከፍል የተወሰነባትን ካሳ የከፈለችው ሱዳን አሁን ሙሉ በሙሉ ሽብርን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር መውጣት ችላለች፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሱዳን ሽብርን ከሚደግፉ ሀገሮች ዝርዝር እንድትወጣ መፈረማቸው ይታወሳል፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ደግሞ በዛሬው ዕለት ሱዳን ሽብርን በመንግስት ደረጃ ከሚደግፉ ሀገራት ተርታ በይፋ እንድትሰረዝ ወስኗል፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት፣ ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሱዳንን ሽብርን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ለመሰረዝ ፊርማቸውን ባኖሩ ጊዜ “የዛሬው ቀን ለሱዳን ታሪካዊ ነው” ማለቱ ይታወሳል፡፡ አሜሪካ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው በታንዛኒያ እና ኬንያ በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች በተፈጸመው የሽብር ጥቃት ከተጎዱ ግለሰቦች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን ለመፍታት ሱዳን በቅርቡ መስማማቷን ተከትሎ እንደሆነም መግለጫው አስታውሷል፡፡
ሱዳን ሽብርን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ለመውጣት 335 ሚሊዮን ዶላር ወደተጎጂዎች አካውንት ማስተላለፏ ይታወሳል፡፡
ከ20 ዓመታት በፊት በታንዛኒያና በኬንያ በሚኘኑት የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ በደረሰው ጥቃት በኤምባሲዎቹ ሲሰሩ የነበሩ አሜሪካውያን መሞታቸውን ተከትሎ አሜሪካ ለጥቃቱ ሱዳንን ተጠያቂ አድርጋ ቆይታለች፡፡ አሁን ታዲያ ሱዳን ከአሜሪካው ሽብርን የሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር በይፋ የተሰረዘች ሲሆን ፣ ሰሜን ኮሪያ ፣ ኢራን እና ሶሪያ በዝርዝሩ የሚገኙ ሀገራት ናቸው፡፡