ወደ ሱዳን የሸሹ የሕወሓት አባላት ኢትዮጵያውያንን ለማስገደል ጉቦ እየሰጡ ነው ተባለ
መንግሥት በሱዳን የሚገኙ ስደተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ ጠንካራ ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ ተጠቁሟል
በማይካድራ የግድያ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ከሰላማዊ ስደተኞች ጋር በሱዳን የስደተኛ ካምፕ አንድ ላይ እንደሚኖሩ ተገልጿል
መንግሥት በሱዳን የሚገኙ ስደተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ ጠንካራ ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ በማይካድራ አሰቃቂ የግድያ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ከሰላማዊ ስደተኞች ጋር በሱዳን የስደተኛ ካምፕ አንድ ላይ እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡
በማይካድራ ላይ አሰቃቂ የግድያ ወንጀል ፈጽመው ወደ ሱዳን የተሰደዱ የሳምሪ ቡድን፣ የሕወሓት ልዩ ኃይል፣ የሕወሓት ፖሊሶችና ደጋፊዎች እንዲሁም ባለሀብቶች በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማስገደል ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ መረጃዎች እንደደረሱት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አስታወቀ፡፡
በሱዳን በስደት ላይ የሚገኙት ሰላማዊ ዜጎች እና ከነጦር መሳሪያቸው የሸሹት የሳምሪ ቡድን ፣ የሕወሓት ልዩ ኃይል ፣ ፖሊሶችና የሕወሓት ደጋፊ ባለሀብቶች አንድ ላይ መሆናቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ ገልጸዋል፡፡
ሰብሳቢው ከትናንት በስቲያ ታኅሳሥ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ሰጥቶ በነበረው መግለጫ ፣ እነዚህ የሕወሓት ኃይሎች “ለሱዳን የፀጥታ ኃይል ጉቦ በመስጠት” ሱዳን በስደት ላይ በሚገኙ ሰላማዊ ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት እንዲደርስ ለማድረግ እየሞከሩ ስለመሆናቸው ነው ለቦርዱ የደረሱ መረጃዎች መነሻ በማድረግ ያስታወቁት፡፡
በዚህም መሰረት በንጹሃን ስደተኞች ላይ እስከ መግደል የሚደርስ ወንጀል ሊፈጸም እንደሚችል የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በቅርበት እንዲከታተል አሳስበዋል፡፡ በተለይ በሱዳን ድንበር አካባቢ ዜጎች ጥበቃ ማግኘት እንዳለባቸውም ነው የገለጹት፡፡
ከስደተኞች መካከል ወደ ሊቢያና ግብጽ የሄዱ ስለመኖራቸው ለሰብሳቢው አቶ ለማ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ይህንን በቀጣይ የምናጣራው ይሆናል” ሲሉ መልሰዋል፡፡
በዳንሻ፣በማይካድራና ሁመራ ጉብኝት ያደረገው ቡድኑ በቀጣይ በራያ፣ በአላማጣ፣ በአክሱም፣ በሽሬ፣ በአድዋ፣ በመቀሌ እስከ ዛላምበሳና ጾረና ድረስ ያሉትን ቦታዎች ምልከታ ያደርጋል ተብሏል፡፡