ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ በፖለቲካና ዲፕሎማሲ አማራጮች ብቻ የሚፈታ መሆኑን ሱዳን ገለፀች
የድንበር ጉዳይ ለሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት እንቅፋት ሊሆን እንደማይገባ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ጀማል አል ሼክ ተናግረዋል
ኢትዮጵያ ግድብ የመገንባት መብት ቢኖራትም ሱዳንን በማይጎዳ መልኩ መሆን አለበት ብላለች
ከኢትዮጵያ ጋር ያለው “የድንበር ውዝግብ የሚፈታው በፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ አማራጮች ብቻ” መሆኑን ሱዳን አስታወቀች።
በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ጀማል አል ሼክ ከአል ዐይን ነውስ ጋር በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ የኢትዮ-ሱዳን የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ እና የሰሜን ጦርነት እንዲሁም የሱዳን ሚና በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለረዥም ዘመናት የዘለቀ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናነቸውና ይህ ግንኙነት በዘላቂነት ማስቀጠል የሱዳን ህዝብና መንግስት ጥልቅ ፍላጎት እንደሆነ ተናግረዋል።
ሀገራቱ ታሪካዊ ግንኙነታቸው ይበልጥ ለማጎልበት በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ የትብብረ ማእቀፎች በጋራ እየሰሩ መሆነቻንም ለአል ዐይን ተናግረዋል።
የኢትዮ ሱዳን ድንበር ጉዳይ
የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ አሁንም በሂደት ላይ ያለ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፤ ሁለቱም ሀገራት የድንበሩ መዘጋት ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች ላይ መፍትሄ ለማበጀት እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
“በጊዜው ድንበሩ ክፍት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ”ም ነው ያሉት አምባሳደሩ።
አምባሳደር ጀማል አል ሼክ፤ አሁን በሱዳን ቁጥጥር ስር ስለሚገኘውና የይገባኛል ጥያቄና ክርክር እየተነሳበት ስላለው ስፍራን በተመለከተ ሱዳን ያላትን አቋም ምን እንደሚመስል ከአል-ዐይን ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል።
“አሁን ክርክር እያስነሳ ያለው መሬት ሱዳን የኔ ነው ብላ ታምናለች” ያሉት አምባሳደር ጀማል፤ ሱዳን ጉዳዩ ከፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ውጭ በሌሎች አማራጮች ይፈታል ብላ እንደማታምንም ተናግረዋል፡፡
“እነዛ ቦታዎች የሱዳን ናቸው፤ ለዚህ መስረጃም እንደፈረንጆቹ 1902 በሁለቱም ሀገራት የተደረሰው ታሪካዊ ስምምነት እንዳለ ይታወቃል፤ ስለዚህም የድንበር ውዝግቡ የስምምነቱን ዋና ዋና ጉዳዮች መሰረት በማድረግ ሊፈታ ይችላል የሚል እምነት አለኝ” ነው ያሉት አምባሳደሩ።
“የሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ለሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት እንቅፋት ሊሆን አይችልም” የሚሉት አምባሳደር ጀማል፤ ሱዳን ጉዳዩን በዲፕሎማሲ እና ፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት ፍላጎት እንዳላት ገልፀዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ በሁለቱም ሀገራት በኩል የድንበሩን ጉዳይ የሚፈታ አካል አለ፣ ጉዳዩ በዚያ መልክ ከተፈታ በኋላ ጉዳዩ ለሁለቱ ሀገራ የኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚያዊ ግንኑነቶችን እንደ አዲስ ለማደስ ያስችላል።
“አሁን ላይ የሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ የተረጋጋ ነው” ያሉት አምባሳደር ጀማል አል ሼክ፤ በቅርቡ የተካሄደው የኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አዋሳኝ ክልሎች ውጤታማ የሰላም እና ልማት ጉባኤ ማካሄዳቸውንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
አምባሳደር ጀማል አል ሼክ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከአል ዐይን ኒውስ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “ኢትዮጵያ ግድብ መገንባትን ጨምሮ ሌሎች የወደፊት የልማት ስራዎችን የማከናወን መብት አላት፤ ይህ ሁሉ የሚሆነው ሱዳንን እስካልጎዳ ድረስ ነው” ብለዋል።
በተለይም ሱዳን ሮሳሪየስ ግድብን ጨምሮ የሱዳን ግማሽ ያህሉ ህዝብ ከዚህ ግድብ ጀርባ የሚኖር በመሆኑ በዚህ ላይ እርግጠኛ መሆን እንደሚፈልጉም አምባሳደር ጀማል ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሱዳን ፍላጎት ገዢ ስምምነት እንዲኖር በመሆኑ፤ በአፍሪካ ህብረት የተጀመረው የማደራደር ጥረት ተጠናክሮ የሶስቱም ሀገራት ፍላጎት ባስጠበቀ መልኩ ስምምነት ላይ እንሚደረስ ተስፋ እንሚያደረጉ አስታውቋል።
“በግድቡ ዙርያ ያለው ትብብር ህጋዊ ማድረግ ለሱዳን በጣም አስፈላጊ እና ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉም ተናረዋል።
የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ግነኙነትን ከማበላሽት ይልቅ የትብብር መንገድ ሊሆን እንደማይችልም አምባሳደር ጀማል አል ሼክ ገልጸዋል።