የሀገሪቱ መንግስት ስለ ህዳሴ ግድብ ድርድር የሚገልጽ ደብዳቤ ለተመድ የጸጥታው ም/ቤት ልኳል
ሱዳን በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገለጸች
ሱዳን በሁለቱ የታችኛው ሀገራት (በግብፅ እና በሱዳን) እና በዋናዋ የአባይ ዉሃ መነሻ ሀገር (ኢትዮጵያ) መካከል የተጀመረውን ድርድር ለማስጀመር ካርቱም እያደረገች ያለችውን ጥረት በተመለከተ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ ፣ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሶስትዮሽ ትብብር አስፈላጊነትን በአጽንኦት ገልፃለች፡፡
ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ግድቡን የተመለከተ ደብዳቤ የላኩት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስማ መሃመድ አብደላ ናቸው፡፡ ሚኒስትሯ በደብዳቤያቸው ከህዳሴ ግድብ ድርድር ጋር በተያያዙ የሀገራቸውን አቋም አብራርተዋል፡፡
የሱዳን የዜና ወኪል ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 25/2012 ዓ.ም እንደዘገበው ደብዳቤው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከግብፅና ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ያደረጉትን ዉይይት ፣ ዉይይቱ እንዲቀጥል የካርቱምን ተነሳሽነት ዝርዝር ሀሳቦች የያዘ ሲሆን ይሄም በዉሃና መስኖ ሚኒስትሮች ደረጃ ድርድሩን ለመቀጠል ስምምነት ላይ እንዲደረስ ማድረጉን ያካትታል፡፡
ደብዳቤው የሱዳንን መሠረታዊ አቋም የሚያረጋግጥ ነው ያለው ዘገባው ይህም በእስካሁኖቹ ድርድሮች የተንጸባረቀ እና በቅንነት በሚደረጉ ድርድሮች ላይ የተመሠረተ ነውም ብሏል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው እና ግብጽ እንደስጋት በምትመለከተው የህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሲደረግ የነበረው ድርድር እንደገና መጀመሩን በደስታ እንደሚቀበል ባለፈው ቅዳሜ ገልጿል፡፡
“ሁሉንም ወገኖች የሚያረካ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሱዳንን በቅን ልቦና የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍም” ህብረቱ አስታውቋል፡፡
በህዳሴ ግድብ የዉሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ዙሪያ በአሜሪካ ግምጃ ቤት በተዘጋጀው ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ላይ ለመምከር በዋሽንግተን በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ አዲስ አበባ አለመሳተፏን ተከትሎ ድርድሩ ተቋርጦ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣዩ የክረምት ወቅት (ከሳምንታት በኋላ) ግድቡን ዉሃ መሙላት እንደምትጀምር እና በክረምቱ 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ዉሃ ለመሙላት መዘጋጀቷን በተደጋጋሚ ይፋ አድርጋለች፡፡
ካይሮ በበኩሏ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ያልፈረሙበት የዋሽንግተኑ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ረቂቅ የስምምነት ሰነድ እንዲተገበር እና ስምምነት ሳይደረስ የግድቡ የዉሃ ሙሌት እንዳይጀመር በመወትወት ላይ ነች፡፡