የሱዳኑ መሪ አልቡርሃን ከኢትዮጵያ ጋር “ጤናማ ግንኙነት እንዲኖረን እንፈልጋለን” አሉ
የአፍሪካ ሕብረት፤ አዲስ አበባ እና ካርቱም በመካከላቸው ያለውን ውጥረት እንዲያረግቡ አሳስቧል
አርቡርሃን ከሰሞኑ ግጭት ወደተነሳበት ኢትዮ-ሱዳን ድንበር አቅራቢያ አልፋሽቃ ሄደው ነበር
ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ጋር ውጥረት ውስጥ የገባችው ሱዳን ከጎረቤቷ ጋር ሰላማዊና ሚዛናዊ ግንኙነት እንድኖራት እንደምትፈልግ አስታወቀች፡፡
የሀገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ም/ቤት ሊቀ መንበር አብዱል ፋታህ አልቡርሃን ከኢትዮጶያ ጋር ጤናማ ግንኙነት እንድኖር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ አል ቡርሃን ይህንን ያሉት ከአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር በካርቱም በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡
የአውሮፓ ሕብረት፤ በአዲስ አበባ እና ካርቱም መካከል ያለውን አለመግባባት ለማርገብ ጥረት እያደረገ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ የሕብረቱ ልዩ መልዕክተኛ አኔቴ ዌበር ሰሞኑን ካርቱም ገብተው ከአል ቡርሃን ጋር ተወያጥተዋል፡፡
ካርቱም ከሰሞኑ ሰባት ወታደሮቿ በኢትዮጵያ እንደተገደሉባት ብትገልጽም አሁን ግን ጉርብትናው ጤናማ እንድሆን ፍላጎት እንዳላት መሪዋ አስታውቀዋል፡፡ ነገርግን የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ መግባቱን እና የፈጸመውን ትንኮሳ ተከትሎ በተፈጠረ ግጭት ህይወት ማለፉን መግለጹ ይታወሳል፡፡
የሱዳን ጦር አዛዥ እና የሃገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘውን የሃገራቸውን ጦር ከሰሞኑ ጎብኝተው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ካርቱም ከሰሞኑ ተገደሉብኝ ያለቻቸው ወታደሮች ድንበር ዘልቀው በመግባታቸው እንደሆነ ገልጾ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዛሬ እለት በትዊተር ገጻቸው እንደጻፉት“በእኛ እና ሱዳን መካከል መፋጠጥ መኖር የለበትም፣ ስሜታችን በመቆጣጠር እና መቆጠብ አለብን” ብለዋል፡፡
ከሱዳን ጋር በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዘላቂ ሰላም እና ለመልካም ጉርብትና ሲባል በአንድነት በመጋፈጥ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፤ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በመካከላቸው “የተፈጠረውን ውጥረት ከሚያባበስ ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ እንዲታቀቡ” አሳስበዋል፡፡