በጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሀን የተመራው ስብሰባው በሀገሪቱ ‘የፀጥታ ጉዳዮች’ ላይ መክሯል ተብሏል
በሱዳን የሽግግር ሉኡላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሀን የሚመራው የወታደራዊና ደህንነት ብሔራዊ ም/ቤት ስብስባ ዛሬ በካርቱም ተካሂዷል፡፡
ስብሰባው በዋናነት በሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ ላይ በተለየ ሁኔታ ደግሞ በምዕራብና ምስራቅ ዳርፉር ወቅታዊ የጸጥታና ደህንነት ሁኔታዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መመክሩን የሱዳን ዜና አግልግሎት /SUNA / ዘግቧል፡፡
የሱዳን መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጀነራል ያሲን ኢብራሂም ያሲን ምክር ቤቱ በቅርቡ በሃገሪቱ በታዩና ለበርካታ ዜጎች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆኑ የፀጥታ መደፍረሶችን መነሻና ያላቸው እንደምታን የተመለከተ ሪፖርት ከሚመለካታቸው አካላት ማድመጡ ገልፀዋል፡፡
መሰል ድርጊቶች ዳግም እንዳይፈፀሙ ለማድረግ ም/ቤቱ ቁልፍ ውሳኔዎችን ማሳለፉንም ጭምር ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት፡፡
የዳርፉርና የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ከሁሉም የሃገሪቱ የፖለቲካ ተዋናዮች የተውጣጡ አባላት ያሉበት የጋራ ወታደራዊ ኃይል ለማደራጀት፣ ህገወጥ የጦር መሳርያ ዝውውርን ለመግታት፣ ትጥቅ ለማስፈታት እና በድንበር አከባቢ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ውሳኔ በምክር ቤቱ መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡
የፀጥታ ኃይል ስምሪት ለማፋጠን ፣ ሰብአዊ እርዳታዎችን ማሳደግ እና አስፈላጊውን ምርመራ በማካሄድ ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ተወስኗልም ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡